በምርጫ ሂደት የተከለከሉ ተግባራት እና የተቀመጡ ቅጣቶች

ሰላም እንደምን ቆያችሁ የበሌ ክ/ከተማ ዓቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት የቴሌግራም ቻናል ተከታዮች እንደሚታወቀው ሀገራችን በቅርቡ ሀገራዊ ምርጫ የምታካሄድ ሲሆን ለዚህም ምርጫ መሳካት የምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ጸድቆ በስራ ላይ የዋለ ሲሆን አዋጁ በምርጫ ወቅት መደረግ ያለባቸው እና የተከለከሉ ተግባራት በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን ለዛሬ የመረጥንላችሁ ርዕስ በምርጫ ወቅት የተከለከሉ ተግባራትና ቅጣቶች በአጭሩ ለማብርርት ተሞክሯል መልካም ንባብ፡፡
በምርጫ ሂደት የተከለከሉ ተግባራት እና የተደነገጉ ቅጣቶች
ማንኛውም ሰው ወይም ድርጅት ከቦርዱ ፈቃድ ውጭ ማንኛውንም የምርጫ ሰነድና ቁሳቁስ ያተመ፣ ያባዛ፣ የፈበረከ ወይም በዚህ መልኩ የተዘጋጀን ህገወጥ የምርጫ ሰነድ እና ቁሳቁስ ይዞ የተገኘ ወይም ያደለ እንደሆነ በእስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል፡፡
በድምጽ መስጫ ዕለት በድምፅ መስጫ ጣቢያ አካባቢ ድምፅ ከመስጠት ወይም የተሰጠን ህጋዊ ተግባር ከማከናወን ውጭ ሌላ ማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ መሳተፍ ወይም ባልተገባ ወይም በተከለከለ ጊዜ የምርጫን ውጤት ማተም፣ ማባዛት፣ ወይም ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጥፋቶች መፈጸም ከብር 90 ሺ እስከ ብር 100 ሺ የሚደርስ በገንዘብ መቀጮ ወይም ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ያስቀጣል፡፡
በቦርዱ ወይም በምርጫ አስፈፃሚዎች ገለልተኝነት ጣልቃ ለመግባት ከሞከረ በተለይም መደለያ ወይም የተስፋ ቃል ከሰጠ ወይም ለመስጠት ከሞከረ፣
ምርጫን ለማወክ ወይም እንዳይካሄድ ለማድረግ ወይም በምርጫው ሂደት ወይም ውጤት ላይ ጫና ለመፍጠር በማሰብ ጥላቻን ወይም ፍርሀትን የሚቀሰቅስ ወይም በምርጫው ሂደት ወይም በምርጫው ውጤት ላይ ጫና የሚፈጥር የሐሰት መረጃ አሳትሞ ያሰራጨ ወይም ለማሰራጨት ሙከራ ካደረገ፣
የምርጫ ሚስጢራዊነትን ከጣሰ፣
ከድምጽ እና ከምርጫ ቁሳቁስ ጋር የተያያዙ ክልከላዎችን ከተላለፈ፣
የቦርዱን ወይም የምርጫ አስፈፃሚዎችን እንቅስቃሴ ካወከ፣
የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ወይም የምርጫ ውጤት አገላለፅ፣
የመራጮች ወይም የፓርቲዎችን መብት አስመልክቶ የተጣሉ ክልከላዎችን ከጣሰ፤ ከብር 30 ሺ እስከ ብር 50 ሺ የገንዘብ መቀጮ ወይም ከስድስት ወር በማያንስ ከአንድ አመት በማይበልጥ ቀላል እስራትይቀጣል፡፡
ማንኛውምሰው:- ሆን ብሎ የቦርዱ፣ የምርጫ ዋና አስፈፃሚው፣ የቦርዱ ሰራተኛ ስልጣኑን ወይም ተግባሩንና ኃላፊነቱን በሚያከናውንበት ወቅት እንቅፋት የሆነ ወይም ያደናቀፈ እንደሆነ፤ ወይም፣
የቦርዱን የስብሰባ ሂደት ሆን ብሎ ያቋረጠ ወይም በነዚሁ ቦታዎች በማንኛውም ሁኔታ ያልተገባ ተግባር የፈፀመ እንደሆነ ወይም ሆን ብሎ በቦርዱ የስራ ቦታ ወይም በመታየት ላይ ባለጉዳይ ላይ በሚሰጠው ውሣኔ ወይም ትዕዛዝ ላይ ተገቢ ያለሆነ ተጽእኖ ለማሳደር ሲባል ማንኛውም የሀይል ተግባር የፈፀመ እንደሆነ፣
በ30 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ ወይም ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ይቀጣል፡፡ አንቀጽ156
ማንኛውም ሰው ምርጫ ከተጀመረበት ቀን አንስቶ ውጤት እስከሚገለፅበት ቀን ድረስ የማንኛውንም እጩ ተወዳዳሪ ፖስተርን ወይም የምርጫ
ማስታወቂያን ያበላሸ፣
ያስወገደ ወይም የቀደደ እንደሆነ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል፡፡ አንቀጽ 158
በህገወጥ መንገድ ዓላማን ማስፋፋት የተከለከለ ስለመሆኑ
የአንድን የፖለቲካ ፓርቲ ዓላማ በኃይል ወይም በማስፈራራት ለማስረጽ ማንኛውንም ሰው ወይም ቡድን ማደራጀት ወይም ማሰልጠን ወይም ሰዎችን በግድ መመልመል በህግ ያስቀጣል፡፡
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተገለፀውን ተግባር ሲፈጸም የረዳ ወይም የተባበረ ማንኛውም ሰው ወይም ቡድን አግባብ ባለው ሕግ ይቀጣል፡፡

በቦሌ ክ/ከተማ ዓቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ
የተዘጋጀ ሰኔ 2013

Comments

Be the first to add a comment