የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው ይዞታዎች ታክስ እንዲከፈልባቸው የሚያስገድድ ሕግ ተዘጋጀ
የተመዘገበ የባለቤትነት መብት በሌለበት ጊዜ ማንኛውም ታክስ የሚከፈልበትን ንብረት ይዘው የሚገኙና በይዞታው ጥቅም የሚያገኙ፣ የይዞታ ማረጋገጫ ባይኖራቸውም፣ የንብረት ታክስ የመክፈል ግዴታ እንዳለባቸው የሚደነግግ አስገዳጅ ሞዴል ንብረት ታክስ አዋጅ ረቂቅ ተዘጋጀ፡፡
አገራዊ ወጥነት ያለው የንብረት ታክስ መሠረት፣ የታክስ ምጣኔና ታክስ የሚከፈልባቸው ንብረቶች እንዲኖሩ ለማስቻል የሚረዳ የአፈጻጸም ሕግ ክልሎች ሊያወጡ እንደሚገባና ለዚህ መነሻ የሚሆን ሞዴል የንብረት ታክስ ሕግ የፌዴራል መንግሥት ማዘጋጀት ስላለበት፣ ገንዘብ ሚኒስቴር ከገቢዎችና ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር ረቂቁን አዘጋጅቶ ይፋ አድርጓል፡፡
ለሁሉም ክልሎችና ለሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተላከው ሞዴል የንብረት ታክስ ሕጉ በሊዝ ይዞታ ስሪት በሚተዳደር ማንኛውም የከተማ ቦታ የመጠቀሚያ መብት፣ ከሊዝ ይዞታ ስሪት ውጪ በሆነ ነባር የቦታ የመጠቀሚያ መብትና ቦታ ላይ በተደረገ ማሻሻያ ወይም በሕንፃ ባለቤትነት ላይ የሚጣልና የሚሰበሰብ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሕጉ መሠረት ታክስ የመክፈል ግዴታ የተጣለበት ማንኛውም ሰው፣ በታክስ ከፋዩ ስም የታክስ ጉዳዮችን እንዲያስፈጽም ውክልና የተሰጠው የታክስ ከፋዩ ተወካይ፣ የሟች የውርስ ንብረትን በሚመለከት ሥልጣን ያለው አስፈጻሚ ወይም አስተዳዳሪ፣ ዕዳ ያለበትን ንብረት በሚመለከት ሥልጣን ያለው ባላደራ፣ ሕንፃውን ወይም ማሻሻያውን የሚያሠራውና የሚቆጣጠረው ኩባንያ፣ የሪል ስቴት የባለቤትነት መብት እስኪያስተላልፍ ወይም የተጠናቀቀውን ሕንፃ ለገዥው በአካል እስኪያስረክብ ድረስ የያዘውን የሚያካትት ይሆናል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የተመዘገበ የባለቤትነት መብት በሌለበት ጊዜ፣ ማንኛውም ታክስ የሚከፈልበትን ንብረት ይዞ የሚገኝ ሰው ወይም በይዞታው ጥቅም እያገኘ ያለ ሰው፣ የይዞታ ማረጋገጫ ባይኖረውም፣ የንብረት ታክስ የመክፈል ግዴታ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡
ሆኖም የተመዘገበ የባለቤትነት መብት በሌለበት ጊዜ ታክሱን እንዲከፍል መደረጉ ብቻውን በንብረት የመጠቀም ወይም ባለቤትነት መብትን እንደማያስገኝና በሌሎች ሕጎች የሚወሰዱ ዕርምጃዎች እንደማያስቀር፣ በተጨማሪም ንብረቱ በጋራ ባለቤትነት ወይም ይዞታ የተያዘ እንደሆነ ሁሉም የጋራ ባለቤቶች ወይም የጋራ ባለይዞታዎች ለንብረት ታክስ በጋራና በተናጠል ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስፍሯል፡፡
ከታክስ ነፃ የመሆን ወይም ዕፎይታ የማግኘት መብቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ከአንድ ንብረት የገበያ ዋጋ ውስጥ ታክስ የሚከፈልበት የንብረቱ የገበያ ዋጋ ሃያ አምስት በመቶ መሆኑንና የመሬት አስተዳደር አካሉ በከተሞች፣ በቦታ መጠቀሚያ፣ በሕንፃዎችና በማሻሻያዎች ምድብ፣ ተፈጻሚነት ባለው የግመታ ዘዴና የዋጋ ግሽበት ማሻሻያዎችን መሠረት ያደረገ ወቅታዊ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለበት ተገልጿል፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በሚያወጣቸው ደረጃዎችና መመርያዎች፣ እንዲሁም የክልሉን የከተሞች ሕግ መሠረት በማድረግ የከተሞች ፈርጅ ምደባና ንዑስ ምደባን እንደሚወስን ተመላክቷል፡፡
የንብረት ታክስ ምጣኔው በመጀመሪያው ዓመት በዝቅተኛ ታክስ ምጣኔ ተጀምሮ በአራት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ጣሪያ ላይ መድረስ በሚያስችል አዳጊ ሒደት ሥራ ላይ እንዲውል እንደሚደረግ፣ የከተማ አስተዳደሮች የታክስ ምጣኔውን በሚያሻሽሉበት ጊዜ የከተማውን ዓመታዊ የካፒታል ወጪ ፍላጎትና የሁሉም ንብረቶች ታክስ የሚከፈልበት ዓመታዊ ዋጋን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባቸው ተደንግጓል፡፡
ዓመታዊ የታክስ ምጣኔው በሚሻሻልበት ጊዜ ከንብረት ጋር ከተያያዙ ገቢዎች በስተቀር፣ ከልዩ ልዩ ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢዎች፣ ከክልሉ መንግሥት የሚገኙ ድጎማዎች፣ የውጭ ዕርዳታና ከሌሎች ምንጮች ከተሞች የሚያገኟቸው ገቢዎች ታሳቢ አይደረጉም ተብሏል፡፡
ዓመታዊ የንብረት ታክስ ምጣኔ ሰንጠረዥ የማፅደቅና የማሻሻል ሥልጣን የተሰጠው ለከተማው ምክር ቤት ሲሆን፣ ምክር ቤት በሌለበት ጊዜ አግባብነት ባለው የክልል ከተማ ሕግ መሠረት ተመሳሳይ ሥልጣን የተሰጠው አካል የማፅደቅና የማሻሻል ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
በከተማ ቦታ መጠቀሚያ መብት ላይ የሚጣለው ታክስ ምጣኔ ታክስ የሚከፈልበት ዋጋ ላይ ከ0.2 በመቶ በታችና ከአንድ በመቶ በማይበልጥ ሁኔታ ተግባራዊ እንደሚደረግ፣ ከተሞች አግባብነት ያላቸውን ሕጎች መሠረት በማድረግ በባዶ ቦታ ላይ ከፍተኛውን የታክስ ተመን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ሰፍሯል፡፡
በሕንፃ ወይም የቦታ ማሻሻያ ላይ የሚጣለው ታክስ ምጣኔ፣ ታክስ የሚከፈልበት ዋጋ ላይ ከ0.1 በመቶ በታችና ከአንድ በመቶ የማይበልጥ መሆኑን፣ ከተሞች ተጠናቀው ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሕንፃዎችና የቦታ ማሻሻያዎች ላይ ከፍተኛውን ታክስ ምጣኔ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡
የንብረቱ ጥቅል ዋጋ በከተማ አስተዳደሮች ከአንድ ሚሊዮን ብር፣ በማዘጋጃ ቤት ከተሞች ከሁለት መቶ ሃምሳ ሺሕ ብርና በታዳጊ ከተሞች ከአንድ መቶ ሺሕ ብር ያነሰ፣ ዝቅተኛ ገቢ ላለው አንድ ቤተሰብ በመኖሪያነት የሚያገለግል የከተማ ቦታ፣ ሕንፃና የቦታ ማሻሻያ ከንብረት ታክስ ነፃ ተደርጓል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ለአምልኮ ተግባርና ለመካነ መቃብር አገልግሎት የሚጠቀሙባቸው ንብረቶች፣ በከተማ ክልል ያሉና ለአንድ ቤተሰብ ፍጆታ ለሚውል የግብርና ሥራ የሚያገለግልና ለኅብረተሰቡ ነፃ የማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች አገልግሎቱን ለመስጠት የሚጠቀሙባቸው ንብረቶች ከታክስ ነፃ ናቸው ተብሏል፡፡
Ethiopian Reporter - ሪፖርተር
Comments
Be the first to add a comment