👉የኩርባ መገንጠያ (ጨጎማ) - ጋሼና መንገድ ፕሮጀክት በተሻለ የግንባታ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል

🚧የተንታ - ጋሼና መንገድ ፕሮጀክት አካል የኾነው የኩርባ መገንጠያ (ጨጎማ) - ጋሼና ክፍል ሁለት መንገድ ፕሮጀክት በተሻለ የግንባታ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ 44 ነጥብ 68 ኪሎሜትር የሚሸፍን ሲኾን፥ ከዚህ ቀደም ከደሴ በወልዲያ በኩል ጋሼና እና ላሊበላ ከተሞች ይደረግ የነበረውን ረጅም ጉዞ የሚያሳጥር ነው። ከዚህም በተጨማሪ ወደ ታሪካዊው የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት እና የሌሎች ገዳማት መዳረሻዎች ምቹ በማድረግ የቱሪስት ፍሰቱን የሚያቀላጥፍ ነው።

በአካባቢው ባለው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት የግንባታ ግብአት እና ማሽነሪዎች አቅርቦት መስተጓጎል፣ በሥራ ተቋራጩ የአቅም እጥረቶች እንዲሁም ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ችግሮች በግንባታው ሂደት ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል።

ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት፣ ተቋማችን ከመሥተዳድር እና ከጸጥታ መዋቅር አካላት እንዲሁም ከሥራ ተቋራጩ ጋር በመኾን ባደረገው የሶስትዮሽ ጥረት፥ የችግሮቹ መጠን በከፊል መቀነስ ተችሏል።

በተለይም የኮን እና ጋሼና ከተሞችን ጨምሮ 12 ኪሎሜትር የሚኾነውን የግንባታው ክፍል ለዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በንዑስ ተቋራጭነት መሰጠቱ፤ ፕሮጀክቱ ከነበረበት ቁመና ጉልህ መሻሻል እንዲያሳይ አግዟል።

በአሁኑ ወቅት በፕሮጀክቱ የአፈር ቁፋሮ፣ የቆረጣና ሙሌት ሥራዎች፣ የውኃ መፋሰሻ ቱቦዎች ቀበራ፣ የሰብቤዝ ማንጠፍ፣ የቤዝኮርስ ጠጠር ማምረት እና የከልቨርት ግንባታ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የመንገድ ግንባታውን ሀገር-በቀሉ ዮቴክ ኮንስትራክሽን በማከናወን ላይ ሲኾን፥ ልህቀት ዲዛይን እና ግንባታ ኮርፖሬሽን የፕሮጀክቱን ጥራት እና ቁጥጥር ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል። ለፕሮጀክቱ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ከፌደራል መንግሥት በጀት ተመድቧል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የማኅበረሰቡን የትራንስፖርት ችግር እና እንግልት ያስቀራል። የጨጎማ፣ ኮን እና ጋሼና ከተሞችን ጨምሮ የተለያዩ ከተሞችን በማስተሳሰር የሕዝብ ለሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ያጠናክራል። 

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር

@etconp

Comments

Be the first to add a comment