የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
የመንግስት ሰራተኞች የስነ-ምግባር ጥሰት እና የዲሲፕሊን እርምጃ አወሳሰድ
መግቢያ
ድስፕሊን የሚለው ቃል ስርዎ ቃሉ እንግሊዝኛ ቢሆንም ለተመሳሳይ አላማ በአማርኛም ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ከቃሉ አግባብ መረዳት እንደሚቻለው፣ ለአንድ ጥፋት የሚወሰድ የቅጣት እርምጃ መሆኑን መገመት ይቻላል። ቅጣት ያለጥፋት አይኖርም ተብሎ ይገመታል። ምንም እንኳን ሁልጊዜ ይህ ግምት ባይሠራም፣ በአመዛኙ ትክክል ይሆናል። ነገር ግን ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ተፈጸመ የተባለው ጥፋት በማስረጃ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ይህ ጠቅላላ አስተሳሰብ እንደተጠበቀ ሆኖ ከርእሱ አጻር፣ መታየት ያለበትን ጉዳይ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 አንቀጽ 96 እና ተከታዮቹ የተደነገገውን ቀጥለን እንመለከታለን።
ዓላማ
የዲስፕሊን ቅጣት ዓላማ የመንግሥት ሠራተኛው በፈጸመው የዲስፕሊን ጉድለት ተፀፅቶ በአመለካከቱና በሥነ-ምግባሩ እንዲታረምና ብቁ ሠራተኛ እንዲሆን ለማስቻል ወይም የማይታረም ሆኖ ሲገኝ ለማሰናበት እንደሆነ በአዲሱ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 አንቀጽ 96 ላይ ተደንግጓል፡፡ የዲስፕሊን ጉድለት የፈፀመ የመንግስት ሰራተኛ እንደ ጥፋቱ ክብደት የቃል ማስጠንቀቂያ፤ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፤ እስከ አሥራ አምስት ቀን ደመወዝ የሚደርስ መቀጮ፤ እስከ ሦስት ወር ደመወዝ የሚደርስ መቀጮ፤ እስከ ሁለት ዓመት ለሚደርስ ጊዜ በሥራ ደረጃ እና ደመወዝ ዝቅ ማድረግ፤ ከሥራ ማሰናበት ቅጣቶች ሊወሰንበት እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 97 ላይ ተደንግጓል፡፡
የዲሲፕሊን ጥፋት አይነቶች
አዋጁ ሁለት አይነት የዲሲፕሊን ጥፋት አይነቶች እንዳሉ ያስቀመጠ ሲሆን ይህም ቀላል እና ከባድ የዲሲፕሊን ጥፋት ናቸው፡፡ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ቅጣቶች ማለትም የቃል ማስጠንቀቂያ፤ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፤ እስከ አሥራ አምስት ቀን ደመወዝ የሚደርስ መቀጮ ለቀላል የዲሲፕሊን ጥፋቶች የሚጣሉ ሲሆን እስከ ሦስት ወር ደመወዝ የሚደርስ መቀጮ፤ እስከ ሁለት ዓመት ለሚደርስ ጊዜ በሥራ ደረጃ እና ደመወዝ ዝቅ ማድረግ፤ ከሥራ ማሰናበት ቅጣቶች ለከባድ የዲሲፕሊን ጥፋቶች የሚጣሉ ቅጣቶች ናቸው፡፡ ከሥራ ደረጃና ደመወዝ ዝቅ በማድረግ የተቀጣ የመንግሥት ሠራተኛ የቅጣት ጊዜውን ሲያጠናቅቅ ሠራተኛው ከሚሰራበት ሥራ መደብ እና ደረጃ ቀጥታ ግንኙነት ባለው ጥፋት ምክንያት ከስራ ደረጃና ደመወዝ ዝቅ ብሎ እንድሰራ ተቀጥቶ ካልሆነ በስተቀር ከመቀጣቱ በፊት ይዞት ከነበረው የሥራ መደብ ጋር ተመሳሳይ ክፍት የሥራ መደብ ካለ ያለምንም ተጨማሪ የደረጃ ዕድገት ሥነ-ሥርዓት፣ ከመቀጣቱ በፊት ይዞት ከነበረው የሥራ መደብ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ክፍት የሥራ መደብ ካልተገኘ ክፍት የሥራ መደቡ በተገኘ ጊዜ ያለምንም ተጨማሪ የደረጃ ዕድገት ሥነ-ሥርዓት፣ በሥራ መደቡ ላይ እንደሚመደብ ተደንግጓል፡፡
በአዋጁ አንቀጽ 97(5) መሰረት የመንግሥት ሠራተኛ በዲስፕሊን ከተቀጣ በኋላ ቅጣቱ በሪከርድነት ሊቆይና ሊጠቀስበት የሚችለው፣ ቀላል የዲስፕሊን ቅጣት ከሆነ ቅጣቱ ከተወሰነበት ቀን ጀምሮ ለሁለት ዓመት፣ ከባድ የዲስፕሊን ቅጣት ከሆነ ቅጣቱ ከተወሰነበት ቀን ጀምሮ ለአምስት ዓመት እንደሆነ ተደንግጓል፡፡
ከባድ የዲስፕሊን ቅጣት የሚያስከትሉ ጥፋቶች ምን ምን እንደሆኑ በአዋጁ አንቀፅ 98 ላይ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ በዚህም፡-
ሕጋዊ ትዕዛዝን ባለማክበር፣ በቸልተኝነት፣ በመለገም፣ ወይም ሆነ ብሎ የአሠራር ሥነ-ሥርዓት ወይም የመንግስትን ፖሊሲ ባለመከተል በሥራ ላይ በደል ማድረስ፤
ጉዳዮችን ሆን ብሎ ማዘግየት ወይም ባለጉዳዮችን ማጉላላት፤
ተቋምን አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር መሠማራት ወይም ሥራ እንዳይሠራ ሆን ብሎ ማወክ ወይም ከሚያውኩት ጋር መተባበር፤
በቀላል የዲስፕሊን ቅጣት እርምጃዎች ባለመታረም ያለበቂ ምክንያት በተደጋጋሚ ከሥራ መቅረት ወይም የሥራ ሰዓት አለማክበር፤
በሥራ ቦታ በጠብ አጫሪነት መደባደብ፤
በልማዳዊ ስካር ወይም በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ በመመረዝ ሥራን መበደል፤
ጉቦ መቀበል ወይም እንዲሰጠው መጠየቅ፤
በሥራ ቦታ ለሕዝብ ሞራል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት መፈጸም፤
የሌብነት ወይም የእምነት ማጉደል ድርጊት መፈጸም፤
የማታለል ወይም የማጭበርበር ድርጊት መፈጸም፤
በመሥሪያ ቤቱ ንብረት ላይ ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት ጉዳት ማድረስ፤
በሥልጣን አለአግባብ መገልገል፤
በሥራ ቦታ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት መፈፀም፤
ከላይ ከተዘረዘሩት ጋር ተመሳሳይ ክብደት ያለው ሌላ የዲሲፕሊን ጉድለት መፈጸም ናቸው፡፡
በሌላ በኩል አዋጁ ከባድ የዲስፕሊን ቅጣት አይነቶችን ቢዘረዝርም ቀላል የዲስፕሊን ቅጣት የሚያስከትሉ ጥፋቶች ግን ምን ምን እንደሆኑ በግልፅ አላስቀመጠም፡፡
የዲስፕሊን እርምጃዎች አወሳሰድ ሥርዓት
ይህ አዋጅ በአንቀጽ 99 ላይ የዲሲፕሊን እርምጃ አወሳሰድ ሥረዓትን ያስቀመጠ ሲሆን በዚሁም መሰረት ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት መደበኛ የዲስፕሊን ምርመራ የሚያካሂድና የውሳኔ ሀሳብ ለመሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ የሚያቀርብ የዲስፕሊን ኮሚቴ ማቋቋም እንዳለበት አዋጁ ያስቀምጣል፡፡ የዲስፕሊን ቅጣት የማንኛውንም ፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይጠብቅ ወይም ሳይከተል ሊወሰን እንደሚችልም በአዋጁ ተደንግጓል፡፡
በዚሁም መሰረት በተቋቋመ የዲሲፕሊን ኮሚቴ አማካኝነት ተጣርቶ የውሳኔ ሀሳብ የቀረበለት የመሥሪያ ቤት የበላይ ኃላፊ በበቂ ወይም አሳማኝ በሆነ ምክንያት የውሳኔ ሀሳቡን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለመቀበል ወይም ውድቅ ለማድረግ ይችላል፡፡ ነገር ግን የማንኛውም መንግሥት መሥሪያ ቤት የበላይ ኃላፊ በዚህ አዋጅ አንቀፅ 98 መሰረት ተቋምን አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር መሠማራት ወይም ሥራ እንዳይሠራ ሆን ብሎ ማወክ ወይም ከሚያውኩት ጋር መተባበር፤ ጉቦ መቀበል ወይም እንዲሰጠው መጠየቅ፤ የሌብነት ወይም የእምነት ማጉደል ድርጊት መፈጸም፤ የማታለል ወይም የማጭበርበር ድርጊት መፈጸም፤ ላይ የተመለከተውን ከባድ የዲስፕሊን ጥፋት መፈፀሙን ካመነ በዲሲፕሊን ኮሚቴው ከባድ የዲስፕሊን ጥፋት የፈጸመው ሠራተኛ ከስራ እንዲሰናበት የቀረበለትን ውሳኔ ሀሳብና ጉዳይ ለመሥሪያ ቤቱ የሥራ አመራር ጉባኤ በማቅረብ ማስወሰን አለበት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሠረት በአንድ መስሪያ ቤት የሥራ አመራር ጉባኤ አማካይነት የተሰጠ ከሥራ የማሰናበት ውሳኔ በዚህ አዋጅ ወይም በሌላ ሕግ በተቋቋመ ማንኛውም አስተዳደራዊም ሆነ መደበኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ ሊታይ አይችልም።
በአዋጁ አንቀጽ 101 መሠረት የመንግስት ሰራተኛ ላይ የዲስፕሊን ክስ ከቀረበ ሰራተኛው ከተጠረጠረበት ጉዳይ ጋር አግባብነት ያላቸው ማስረጃዎችን በማበላሸት፣ በመደበቅ ወይም በማጥፋት ምርመራውን ያሰናክላል ወይም በመንግስት ንብረት ላይ ተጨማሪ ጉዳት ያደርሳል፣ ከተከሰሰበት ጥፋት ክብደት አንፃር የሌሎችን ሰራተኞች ሞራል የሚነካ ወይም ተገልጋይ ሕዝብ በመስሪያ ቤቱ ላይ ሊኖረው የሚገባውን እምነት ያዛባል ወይም ተፈፀመ የሚባለው ጥፋት ከስራ ያሰናብተዋል ተብሎ ሲገመት ከስራ ታግዶ እንዲቆይ የሚደረግ መሆኑን አዋጁ ደንግጓል፡፡ በዚህም አንድ ሰራተኛ ከስራና ከደመወዝ ታግዶ ሊቆይ የሚችለው ከሁለት ወር ለማይበልጥ ጊዜ ሲሆን የመንግስት ሰራተኛው በተከሰሰበት የዲሲፕሊን ጉድለት ምክንያት ከስራ እንዲሰናበት ካልተወሰነበት በስተቀር በእግዱ ወቅት ሳይከፈለው የቀረው ደመወዝ ያለ ወለድ ልከፈለው እንደሚገባም ተደንግጓል፡፡
መጠነ ሰፊ የዲስፕሊን ችግር ያለበት መሥሪያ ቤት ላይ የሚወሰድ ልዩ የዲሲፕሊን እርምጃ ፡-
Comments
Be the first to add a comment