የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
አግባብ ባለዉ ድንጋጌ አስገዳጅነት የሚረጋገጡና የሚመዘገቡ ሰነዶች ህጋዊ ዉጤትን በተመለከተ
አግባብ ባላቸው ሕግ መሠረት ካልተረጋገጡ እና ካልተመዘገቡ ሕጋዊ ውጤት የማያገኙ ሠነዶችን አስመልክተው ከፍትሐብሔር ሕግ ከተመላከተው አንቀጾች በተጨማሪ ለጠቅላላ ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ከዚህ በታች ባሉት የተለያዩ የፌዴራል አዋጆች እና ደንቦች ላይ ጭምር የተቀመጡ ስለመሆናቸው ለማሳያ ይረዳ ዘንድ እንደሚከተለዉ ተቀምጧል፡፡
1. ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1123/2013 የኢትዮጵያ ንግድ ሕግ “ባለ አንድ አባል ኃ/የተ/የግ/ማሕበር ለመቋቋም አባሉ የሚሰጠው መግለጫ ሰነድ ለማረጋገጥ እና ለመመዝገብ ስልጣን በተሰጠው አካል ፊት መደረግ እንዳለበት (በአንቀጽ 536 ንኡስ ቁጥር 1) የሚያመላክት ሲሆን እንዲሁም ይህ ባለ አንድ አባል ያለው ማሕበር ለመቋቋም በቅድመ ሆኔታ ዕጩ ንብረት ጠባቂ አስመልክቶ አባሉ እና ዕጩነቱን ከተቀበለው ንብረት ጠባቂ ጋር የሚያደርጉት ስምምነት በተመሳሳይ ሁኔታ በውል አዋዋይ አካል ፊት ቀርቦ ካልተረጋገጠ ባለ አንድ አባል ኃ/የተ/የግ/ ማሕበር ሊመሠረት እንደማይችል (በንግድ ሕጉ አንቀጽ 537(1) አስገዳጅ ድንጋጌ ተቀምጠዋል።
2. በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት አዋጅ ቁጥር 1180/2012 ለማስፈጸም በወጣው ደንብ ቁጥር 474/2012 ዓ.ም
• በትግበራ ላይ የሚገኝ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ለሌላ 3ኛ ወገን በሽያጭ ለማስተላለፍ (በደንቡ አንቀጽ 12) የሚደረግ ስምምነት፣
• በቴክኖሎጂ ተቀባይ እና አቅራቢ መካከል የሚደረግ የቴክኖሎጂ ስምምነት ለመፈጸም (አንቀጽ15/1/ሰ/) እና
• ከውጭ ንግድ ጋር በተያያዘ በአገር ውስጥ ባለሀብቱ እና በውጭ ኢንተርፕራይዝ መካከል የሚደረግ ስምምነቶች (በደንቡ አንቀጽ 16 ንዑስ ቁጥር 1 (ሰ)
ከላይ የተዘረዘሩ ስምምነቶች እንደ ቅድመ ሁኔታ ሰነድን ለማረጋገጥ እና ለመመዝገብ ስልጣን በተሰጠው አካል ፊት ተረጋግጠው ካልተመዘገቡ በቀር በሕግ ፊት ተቀባይነት እንደማገያኙ አስገዳጅ ድንጋጌ ናቸዉ
3. በተመሳሳይ የንግድና ምዝገባ ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 ለማስፈጸም በወጣው የሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁጥር 392/2009 ዓ.ም በአንቀጽ 37 እና 48 ላይ እንደተቀመጠው
• የሆልዲንግ ኩባንያ ልዩ የምስክር ወረቀት ለማግኘት በቅድመ ሁኔታ በሆልዲንግ ኩባንያው የቡድን አባላት መካከል ኩባንያው ስለመመስረቱ የሚደረግ ስምምነት (አንቀጽ 37 ንዑስ ቁጥር 1 ላይ እንደተቀመጠው) እንዲሁም
• የፍሬንቻይዚንግ ልዩ የምዝገባ የምስክር ወረቀት ለማግኘት የፍሬንቻይዘሩ (ውል ሰጪ) እና የፍሬንቻይዝ (ውል ተቀባይ) መካከል የተፈጸመ የፍሬንቻይዚንግ ውል ስምምነት (አንቀጽ 48 እንደተመለከተው)
በቅድመ ሁኔታ ሰነድን ለማረጋገጥና ለመመዝገብ በሕግ ስልጣን በተሰጠው አካል ፊት ቀርበው ካልተረጋገጡና ካልተመዘገቡ ሕጋዊ ውጤት እንደማይኖራቸው ተደንግጓል።
4. በሌላ በኩል ሠነድን ለማረጋገጥና ለመመዝገብ በወጣው አዋጅ ቁጥር 922/2008 አንቀጽ 9(1) እንደተመላከተው ካልተረጋገጠና ካልተመዘገበ ሕጋዊ ውጤት አይኖራቸውም ተብሎ ከተገለጹት መካከል የውክልና ስልጣን መስጫ ሰነድ ብቻ ሳይሆን የውክልና መሻሪያ ሰነድም አንዱ ሲሆን የመሻሪያ ሰነድ ወካይን ከመቼ ቀንና ዓ.ም ጀምሮ ከስልጣኑ እንደሻረው እና ከተሻረ ጊዜ ጀምሮ በወካይ ስም አንዳች ሕጋዊ ተግባር እንዳይፈጸም በተሻረው የውክልና ስልጣን እንዳይሰራ አስቀድሞ ለመከላከል የመሻሪያው ሰነድ ስልጣን ባለው አካል ተረጋግጦ መመዝገብ እንዳለበት ተደንግጎ ይገኛል።
ምንጭ፣ Federal Documents Authentication and Registration Agency.
ኦምኒኤል (ህዳር 13/2014 ዓ.ም)
Comments
Be the first to add a comment