የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
ሰላም! እንዴት ከርማችኋል!
ምንም አይነት እውቀት፣ ክህሎት፣ የስራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት ቢኖራቸውም እንኳን የመንግስት ሰራተኞች መሆን የማይችሉ ሰዎች እንዳሉ ያውቃሉ?
እንግዲያውስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 56/2010 ዓ.ም በአንቀጽ 14 የመንግሥት ሠራተኛ ሆነው ሊቀጠሩ ስለማይችሉ ሰዎች የደነገገውን ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፤
ሀ) ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ሰው፤
ለ) ቅጣቱ ከተፈጸመ፣ በይርጋ ከታገደ ወይም በይቅርታ ከተሠረዘ በኋላ 5 ዓመት ያለፈው ካልሆነ በስተቀር የሙስና፣ የእምነት ማጉደል፣ የስርቆት፣ የማጭበርበር ወይም የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽሞ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት የተፈረደበት ማንኛውም ሰው፤
ሐ) የብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ የሌለው ሰው፤
መ) በሕግ በተደነገገው መሠረት ቃለ-መሀላ ለመፈጸም ፈቃደኛ ያልሆነ ሰው፤
ሠ( ከሥራ ከተሰናበተ ጊዜ ጀምሮ አምስት ዓመት ካልሞላው በስተቀር ከማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት በዲስፕሊን ጉድለት ምክንያት ከሥራ የተሰናበተ ሰው፤
የመንግስት ሰራተኛ ሆኖ ሊቀጠር አይችልም።
በመሆኑም ማንኛውም ሰው በመንግሥት ሥራ ተቀጥሮ ለማገልገል ብቁ መሆኑን ለማረጋገጥ፥
ሀ) ከኤች.አይ.ቪ./ኤድስ ምርመራ በስተቀር የጤንነት ማረጋገጫ የሕክምና ምርመራ እና
ለ) ከሙስና፣ ከእምነት ማጉደል፣ ከስርቆት፣ ከማጭበርበር ወይም ከአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ነጻ መሆኑን የሚያረጋግጥ ከፖሊስ የተሰጠ ማስረጃ
የማቅረብ ግዴታ አለበት።
ታህሳስ 14 ቀን 2015 ዓ.ም
ፋሲካ አጌና (የህ/ስ/ም/መ/ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ አቃቤ-ሕግ)
Comments
Be the first to add a comment