ሰላም እንዴት ሰነበታችሁ በዛሬዉ ጽሁፋችን በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ መሰረት በመንግሥት የዉጭ ደህንነት እና በመከላከያ ኃይል ላይ የሚደረጉ ወንጀሎችን ከሚያስከትሉት ኃላፊነት/ተጠያቂነት ጋር አቅርበንላችኋል መልካም ንባብ
በአገር ነጻነት ላይ የሚደረግ ወንጀል፡-
ማለት የአገሪቱን ነጻነት አደጋ ላይ ለመጣል ወይም አገሪቱ ሉአላዊነቷን እንድታጣ፤ የዉጭ መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ለመገፋፋት፤ የዉጭ መንግሥት የጠላትነት ድርጊት በአገሪቱ ላይ እንዲፈጽም/ አገሪቱ ከዉጭ አገር መንግሥት ጋር ጦርነት እንድትዋጋ/ የጠላትነት ድርጊት እንዲፈጸምባት፤ በጠላትነት እንድትከበብ/እንድትያዝ በማሰብ ማንኛዉንም ድርጊት ማድረግ ነዉ፡፡
የአገር መከላከያ ኃይልን መጉዳት፡-
ማለት ማንም ሰዉ አስቦ ወታደራዊ ጠባይ ያለዉን/ ለአገር መከላከያ እንዲሆን የታቀደዉን ማንኛዉንም የኢኮኖሚ ድርጅት የመከላከያ ሥራ ተቋም/ ሥፍራ የመገናኛ/ የመጓጓዣ ዘዘዴ ሥራ ማከማቻ የጦር መሣሪያ ወይም ቁሳቁስ ያለአግባብ አሳልፎ በመስጠት በማፍረስ የተንኮል ሥራ በመፈጸም/ ለአገልግሎት እንዳይዉል በማድረግ፤
ጠላት ለሆነ ለዉጭ አገር መንግሥት ወታደሮች በማቅረብ/ የኢትዮጵያ ዜጎች ለዚሁ ለጠላት አገር በወታደርነት እንዲያገለግሉ በመመልመል/ በማግባባት/ ራሱ ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለዚሁ ዓይነት የጠላት አገር መንግሥት በመሰለፍ፤
የጦር ወታደሩ የጦር አገልግሎቱን ከመፈጸም እምቢተኛ እንዲሆን ወታደራዊ አመጽ እንዲያስነሳ/ እንዲከዳ በግልጽ በማነሳሳት/ ጦር ወታደርነት ግዴታ ያለበት ሰዉ ከነዚህ ወንጀሎች አንደናዉን እንዲፈጽም/ እንዲነሳሳ በማድረግ እና ለአገር መከላከያ የሚያገለግሉትን ወታደራዊ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በማሰናከል በማበላሸት/ በማናቸዉም ሌላ ዘዴ የተንኮል ድርጊት በመፈጸም በኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል ላይ ጉዳት ማድረስ ነዉ፡፤
ከፍ ያለ ክዳት፡-
ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የሆነ ወይም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንዲያስከብር በግልጽ አደራ የተጣለበት ሰዉ የጦር መሣሪያ በመያዝ/ በጸብ ድርጊት ኢትዮጵያን ከተቃወመ፤ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ከሚያደርግ ኃይል ጋር/ ለዚሁ ኃይል ጥቅም ከሚሠራ ሰዉ/ ድርጅት ጋር በመተባበር/ ምስጢራዊ ግንኙነት በማድረግ ይኸዉ ኃይል እንዲመቸዉና እንዲቀናዉ በማናቸዉም አኳኋን ከረዳ ወይም ዕቃዎችን የጦር መሣሪያዎችን ፕላኖችን ማስረጃ የሚሆኑ ጽሁፎችን/ ለአገሩ መከላከያ ሚያገለግሉትን ማንኛዎቹንም ነገሮች በቀጥታ/ በእጅ አዙር ለጠላት አሳልፎ በመስጠት/ በአገልግሎቶችና ይህን የመሳሰሉ ዕቃዎችን ለጠላት በማቅረብ ጠላትን ከደገፈ ከፍ ያለ ክዳት እንደፈጸመ ይቆጠራል፡፡
ክዳት፡-
ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የሆነ ወይም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንዲያስከብር በግልጽ አደራ የተጣለበት ሰዉ አስቦ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ በምስጢር እንዲጠበቅና እንዳይገለጽ የተደረገዉን ምስጢር ሰነድ የመላላክ ጉዳይ/ አንድ ዉሣኔ ለሕዝብ/ ለዉጭ አገር መንግሥት የፖለቲካ ድርጅት፤ ሌላ ድርጅት/ ወኪል የገለጸ አሳልፎ የሰጠ፤ ወሬዉን ያስተላለፈ/ በግልጽ እንዲነገር ማድረግ፤
የእትዮጵያ መንግሥት እንደራሴ/ መልዕክተኛ ሆኖ ከዉጭ አገር መንግሥት ጋር እንዲፈጽም የተላከበት/ ለኢትዮጵያ ጥቅም ሊከራከርበትና ሊፈጽም የሚገባዉን ጉዳይ ግልጽ በሆነ ዓይነት እንዲሰናከል ያደረገ እንደሆነ/ የኢትዮጵያን ደህንነት ነጻነት/ ዋነኛ ጥቅሞችን የሚመለከቱትን ሰነዶች፤ ጽሁፎች/ ማስረጃዎች ያበላሸ ያጠፋ ደበቀ እንዲጠፉ ያደረገ/ ወደ ሐሰተኛነት መለወጥ ነዉ፡፡
የኢኮኖሚ ክዳት፡-
ማለት ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ወይም የኢትዮጵያን ጥቅም እንዲያስከብር በግልጽ አደራ የተጣለበት ሰዉ አስቦ ስለኢትዮጵያ/ ስለመከካከያ ኃይል ከፍተኛ ጥቅም ሲባል በምስጢር የሚጠበቀዉን ኢኮኖሚያዊ ጠባይ ያለዉን የመላላክ ግንኙነት፤ ዉሣኔ፤ የተደረገ ነገር/ ሰነድ ለሕዝብ/ ለዉጭ አገር ሰዉ የገለጸ አሳልፎ የሰጠ ይዘቱን ያስተላለፈ/ እነዚሁ እንዲያገኙት ሲያደርግ
እንዲጠብቃቸዉ በኃላፊነት የተሰጡትን ዕቃዎች መሣሪያዎች/ እነዚህን የመሳሰሉትን ሌሎች ነገሮች የገለጸ/ አሳልፎ የሰጠ እንደሆነ/ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት የሚያደርግ መንግሥት ባወጣዉ ብድር ጉዳይ የተካፈለ/ ለብድሩ የሚዉል ገንዘብ/ ንብረት ሲያዋጣ የኢኮኖሚ ክዳት እንደፈጸመ ይቆጠራል፡፤
ከጠላት ጋር መተባበር፡-
ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የሆነ/ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንዲያስከብር በግልጽ አደራ የተጣለበት ሰዉ ኢትዮጵያ በጦርነት ላይ በምትገኝበት ጊዜ/ ግዛቷ በሙሉ ወይም በከፊል በጠላት በተወረረረበት ጊዜ የጠላትን ዓላማ ለማሳካት በማሰብ በምክርም ሆነ በተግባር ጠላትን መደገፍ ከጠላት ጋር የመተባበር ድርጊት ነዉ፡፡
ስለላ፡- ማንም ሰዉ ለአንድ የዉጭ አገር መንግሥት/ ለአንድ የዉጭ አገር የፖለቲካ ድርጅት/ ለማንኛዉም ሌላ የዉጭ አገር ድርጅት ጥቅም ሲል በኢትዮጵያ በተቋሞቿ በድርጅቶቿ/ በዜጎቿ ላይ ጉዳት በሚያደርስ ሁኔታ የፖለቲካ፤ የዲፕሎማሲ የወታደራዊ/ የኢኮኖሚ ስለላ ሥራ አገልግሎት ያደራጀ በዚሁ ሥራ ተካፋይ የሆነ/ የደገፈ/ የቀጠረ/ ለዚሁ ስለላ የሚያገለግል መረጃ የሰበሰበ ያስተላለፈ ወይም እንዲገኝ ያደረገ/ በምስጢር የሚጠበቀዉንና በሕዝብ በይፋ የማይተወቀዉን መረጃ በመንግሥት/ በግል ለተቋቋሙ መሥሪያ ቤቶች/ ወኪሎቻቸዉ እንዲገለጽ ያደረገ እንደሆነ የስለላ ድርጊት እንደፈጸመ ይቆጠራል፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ መሰረት በመንግሥት የዉጭ ደህንነት እና በመከላከያ ኃይል ላይ የሚደረጉ ወንጀሎች ስር ከአንቀጽ 246 እስከ 252 ድረስ እነዚህ ከላይ የዘረዘርናቸዉ ሰባት የወንጀል ድርጊቶች ሲሆኑ እንደየወንጀሎቹ አይነትና እንደነገሩ ሁኔታ የሚከተሉትን ቅጣቶች የሚያስከትሉ ይሆናል፡፡
- ከ5 ዓመት እስከ 25 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት፤ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት፤ ሞት
- ከ 15 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት
- ከ10 ዓመት እስከ 25 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት፤ ከ6ወር ያላነሰ ቀላል እስራት እስከ 5 አመት ጽኑ እስራት የሚያስቀጡ ይሆናል፡፡
ህድአት ጌታቸዉ ታህሳስ 9/2013 ዓ.ም

Comments

Be the first to add a comment