የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
ኑዛዜ መሻር
• ተናዛዡ ቀድሞ ያደረገውን ኑዛዜ ሽሮታል ሲባል በግልፅና በማያሻማ አኳኋን ሕጋዊ ውጤት ወይም ዋጋ እንዳይኖረው አድርጎታል ማለት ነው፡፡
ኑዛዜ የሟች ጥብቅ የሆነ የግል ጠባይ ያለው እና ራሱ የሚተገብረው ነው፡፡ በመሆኑም የተናዛዡ ሀሳብና ፍላጐት በጥንቃቄ ልንከተለው የሚገባው ነው፡፡ የፍ/ሕ/ቁ. 898(1) ተናዛዡ ኑዛዜዎቹ ዋጋ ያላቸው እንዲሆኑ በሚያስፈልገው ፎርም ዓይነት ግልፅ አድርጎ በማስታወቅ ኑዛዜውን የሻረ እንደሆነ በጠቅላላው አኳኋን የሚሻር ይሆናል ይላል፡፡ በዚሁ ሕግ አንቀፅ 899(1) ተናዛዥ የተናዘዘውን ለመሻር ወይም ለመለወጥ ያለውን ሀሳብ በቂ አድርጎ በመግለፅ ይህንን በኑዛዜው የተመለከተውን ቃል መሻር ይችላል በማለት ተደንግጓል፡፡ ሁለቱም ድንጋጌዎች አንዱ ሌላኛውን በሚያጠናክር መልኩ የተቀመጡ እንጂ የሚቃረኑ አይደለም፡፡
ይህም ሲባል ሁለቱም አንቀፆች ተናዛዡ ያደረገውን ኑዛዜ መሻር ሲፈልግ ሀሳቡን በማያሻማ አኳኋን ግልፅ በሆነ መንገድ መሻር እንደሚችል የሚገልፅ ነው፡፡ ይህም የሚያመለክተው ሟች (ተናዛዡ) ከዚህ ውጭ ሊከተላቸው የሚገባው ሥርዓት መኖሩን አይደለም፡፡ ይልቁንም ተናዛዡ ኑዛዜውን ለመሻር ሊከተላቸው የሚገባውን አማራጮች የሚያመለክት (የሚገልፅ) ነው፡፡ ስለሆነም የኑዛዜ መሻሪያ ሰነዱ ተናዛዥና በቦታው ለነበሩ ምስክሮች የተነበበላቸው ስለመሆኑ የሚያመለክት ቃል በሰነዱ ላይ አለመስፈሩ ኑዛዜው ሕጉ አግባብ እንዳልተሻረ አያስቆጥረውም፡፡
ሰ/መ/ቁ. 96364 ቅጽ 17፣ ፍ/ህ/ቁ. 881፣ 898(1)፣ 899(1)
ፌናን ተጊበሉ
ሕዳር 14/2014 ዓ.ም
Comments
Be the first to add a comment