የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት(ባለ ሀብትነት) ምስክር ወረቀት ስላለው ሕጋዊ ውጤት

የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ምስክር ወረቀት በአጭሩ ለመግለጽ አንድ ሰው የማይንቀሳቀሰውን ንብረት
በባለሀብትነት/በባለቤትነት/ ስለመያዙ የሚያስረዳ ማስረጃ ነው። በፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 1195(1) ላይ
በግልጽ እንደተደነገገው የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በሚመለከት ከአስተዳደር ክፍል የሚሰጠው ምስክር ወረቀት
የንብረቱ ባለሀብት እንደሆነ ግምት ያስወስዳል። ከዚህ ድንጋጌ መረዳት እንደሚቻለው የማይንቀሳቀስ ንብረት ምስክር ወረቀት የንብረቱ ባለሀብት ስለመሆን ግምት ለመውሰድ የሚረዳ እንጂ የማይስተባበል የመጨረሻ ማስረጃ ተደርጎ የሚወሰድ አለመሆኑን ነው። በሌላ በኩል በፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቅጽ 13 መ/ቁ 67011 ላይ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሀብትነትን አስመልክቶ የሚሰጥ የባለቤትነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ተገቢውን ስርዓት እና ደንብ በመከተል የተሰጠ መሆን ያለበት ስለመሆኑ ትርጉም የተሰጠ ሲሆን የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ግምት መውሰጃ የሆነው ምስክር ወረቀት ደንብና አሰራርን መሠረት ባላደረገ እንዲሁም ከስልጣን ውጪ የተሰጠና በሕግ ፊት የማይፀና ስለመሆኑ በማናቸውም ማስረጃ ለማረጋገጥ የተቻለ እንደሆነ በተሰጠው የምስክር ወረቀት የተፈጠረውን የሕጉን የህሊና ግምት ማፍረስ የሚቻል ስለመሆኑ ውሳኔ ተሰጥቷል። በተመሳሳይ መልኩ በፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቅጽ 11 መ/ቁ 47139 ላይ የማይንቀሳቀስ ንብረት ጋር በተያያዘ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ስመ ሃብት ይዞ መገኘት የንብረቱ ባለቤት አድርጐ የማያስቆጥር ስለመሆኑ ውሳኔ ተሰጥቶበታል።


ፌናን ተጊበሉ
ሕዳር 14/2014 ዓ.ም

Comments

Be the first to add a comment