ከገቢ ግብር ነፃ የሆነ ገቢ
****************************
የሚከተሉት ገቢዎች ከገቢ ግብር ነፃ ናቸው፡-
ሀ) ሚኒስትሩ በዚህ ፊደል ተራ በቁጥር (2) ፣ (3) ፣ (4) እና (6) በተመለከቱት ላይ በሚያወጣው መመሪያ የሚያደርገው ገደብ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለተቀጣሪው የሚከፈሉ የሚከተሉት ገቢዎች ከገቢ ግብር ነፃ ናቸው፡-
(1) ሠራተኛው ሲታመም አሠሪው ለሠራተኛው ህክምና አገልግሎት የከፈለለት ገንዘብ፤
(2) በሥራ ውል መሠረት ለሠራተኛው የሚከፈል የትራንስፖርት አበል፤
(3) በሥራ ቦታው ወይም በሥራ ሁኔታው አስቸጋሪነት ምክንያት ለሠራተኛው የሚከፈል አበል፤
(4) ሠራተኛው ከመደበኛ ሥራው ውጪ ሥራውን ለማከናወን ሲንቀሳቀስ የሚከፈለው የመጓጓዣ ወጪ እና የውሎ አበል፤
(5) የመጓጓዣ ወጪው በቅጥር ውሉ መሠረት የተከፈለ ከሆነ ከሥራ ቦታው ውጪ ተመልምሎ ለተቀጠረ ሠራተኛ ወደ ሥራው ሲመጣ ወይም ሥራውን አጠናቆ ሲመለስ የሚከፈለው የመጓጓዣ ወጪ፣ እንዲሁም የውጭ ሀገር ሠራተኞች ከሀገራቸው ሲመጡና ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የሚከፈል የመጓጓዣ ወጪ፤
(6) የማዕድን ማውጣት፣ የማኑፋክቸሪንግ እና የግብርና የንግድ ሥራ የሚሠራ ቀጣሪ ለተቀጣሪው በነፃ የሚያቀርበው ምግብና መጠጥ፤
(7) የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በውጭ አገር ለሚመድባቸው ሠራተኞች የሚከፈል አበል፤
ለ) የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወይም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የቦርድ አባል ወይም ፀሐፊ እንዲሁም የፌደራልና የክልል መንግሥታት ወይም የከተማ አስተዳደሮች በሚያቋቁሟቸው የጥናት ቡድኖች አባል ወይም ፀሐፊ በመሆን የሚከፈል አበል፤
ሐ) ለሠራተኛው ጥቅም ተብሎ ከተቀጣሪው የወር ደመውዝ 15% (አሥራ አምስት በመቶ) ባልበለጠ መጠን በየወሩ በቀጣሪው የሚዋጣ የጡረታ መዋጮ ወይም የፕሮቪደንት ፈንድ፤
መ) በመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ እና በግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ ከግብር ነፃ የተደረገ የጡረታ ገቢ፤
ሠ) የኢትዮጵያ የፌደራል፣ የክልል ወይም የአካባቢ መንግሥታት ወይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከመደበኛ ሥራዎቻቸው ጋር በተያያዘ የሚያገኙት ገቢ፤
ረ) በዓለም ዐቀፍ ስምምነት መሠረት ከግብር ነፃ የሆነ የገቢ መጠን፤
ስ) በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በተደረገ ስምምነት መሠረት ማናቸውም ገቢ ከግብር ነፃ የሚሆነው የሚከተሉት ሁኔታዎች ተሟልተው ሲገኙ ነው፡-
(1) ስምምነቱ የተደረገው ለመንግሥት የገንዘብ፣ የቴክኒክ፣ ሰብአዊ ወይም አስተዳደራዊ እርዳታ ለማቅረብ የሆነ እንደሆነ፤
(2) ከግብር ነፃ ማድረግ የሚያስችለውን አንቀጽ በሚመለከት ሚኒስትሩ መስማማቱን በጽሁፍ ሲገልጽ፤
ሽ) በማንኛውም መስክ ለላቀ የሥራ ክንውን የሚሰጥ ሽልማት፤
ቀ) በተቀባዩ ላይ በደረስ ጉዳት ወይም በሌላ ሰው ሞት ምክንያት የሚከፈል ካሳ፤
በ) የመቀጠር፣ የኪራይ ወይም የንግድ ሥራ ገቢ ካልሆነ በስተቀር በስጦታ ወይም በውርስ የሚገኝ ጥሬ ገንዘብ ወይም ሀብት፤
ተ) በትምህርት ተቋም ውስጥ ትምህርትን በነፃ ለመከታተል የሚፈፀም ክፍያ፤
ቸ) ለቀለብ ወይም ለህፃናት ድጋፍ የሚሰጡ ክፍያዎች፤
ን) ድርጅቱ ከተቋቋመበት ዓላማ ጋር የማይገናኝ የንግድ ሥራ ገቢን ሳይጨምር ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት የሚያገኘው ገቢ፤
ነ) ገንዘብ በሚቆጠርበት ጊዜ ለሚደርሰው ጉድለት ማካካሻ በሚሆን መጠን ብቻ ቀጣሪው ለተቀጣሪው የሚከፍለው እና ለዚሁ ዓላማ መዋሉ የተረጋገጠ የጥሬ ገንዘብ ማካካሻ ክፍያ፤
ኘ) በኢትዮጵያ ፀንቶ በሚሰራበት ሕግ መሠረት በተለይ ከገቢ ግብር ነፃ የተደረገ ገቢ፤
አ) ለመኖሪያ ቤት ሠራተኞች የሚከፈል ደመወዝ፤
ከ) በነዳጅ ሥራ ላይ የተሰማራ ሥራ ተቋራጭ ለንዑስ ሥራ ተቋራጮች የሚፈፅመው ክፍያ::

Comments

Be the first to add a comment