👉አከራዮች በራሳቸው ፍላጎት የቤት ኪራይ መጨመር አይችሉም ተባለ

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የአከራይና ተከራይ ግንኙነትን በቴክኖሎጂ ለማዘመን በጀመረው የዲጂታል ምዝገባ ሂደት እስካሁን 500 ሺህ የሚጠጉ ቤቶችን ወደ ሲስተሙ አስገብቷል።

የቢሮው ኃላፊ ቅድስት ወ/ጊዮርጊስ እንደገለጹት፤ ይህ አዲስ አሰራር አከራዮች መረጃ እንዳይደብቁ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ያለአግባብና ያለ ምንም ምክንያታዊ መነሻ ይደረግ የነበረውን የዋጋ ጭማሪ ሙሉ በሙሉ ያስቀራል።

በአዲሱ ሕግ መሠረት አከራዮች በራሳቸው ፍላጎት ብቻ ዋጋ መጨመር የማይችሉ ሲሆን፣ መንግሥት በየዓመቱ ሰኔ 30 ላይ በሚያወጣው ይፋዊ መግለጫና የገበያ ጥናት መሠረት ብቻ ጭማሪው በፐርሰንት (በመቶኛ) ይወሰናል።

የውል ጊዜው በማብቃቱ ምክንያት ብቻ አከራዮች ተከራይን አስወጥተው ሌላ ሰው ቢያስገቡ እንኳ ዋጋ ጨምረው ማከራየት ስለማይችሉ ተከራዮች ሊሰጉ እንደማይገባ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት የውል ማደስ ሥራውን ሙሉ በሙሉ በኢንተርኔት (ኦንላይን) ለማከናወን ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን፣ አከራይና ተከራይ ዋጋ ሳይጨመርበት ባለው ስምምነት መቀጠል ከፈለጉ ውላቸውን በቀላሉ ማደስ ይችላሉ።

በአጠቃላይ በየሁለት ዓመቱ የኪራይ ውልን በተገቢው መንገድ ማደስ ግዴታ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊዋ፣ አብዛኞቹ ውሎች ጊዜያቸው የሚያበቃው ከሰኔ 30 በኋላ በመሆኑ በውል ስምምነት ውስጥ እያሉ ዋጋ መጨመር ፈጽሞ የተከለከለ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ተከራዮች አከራዮች ዋጋ ጨምሩ ስላሏቸው ብቻ ያለምንም ሕጋዊ መነሻ ክፍያ መጨመር እንደሌለባቸውና መብታቸውን ሊያውቁ እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን፤ መንግሥት ዘላቂ ችግሩን ለመፍታት የጀመረውን የቴክኖሎጂ ማሻሻያ አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት አስታውቋል።

Via AMN

@etconp

Comments

Be the first to add a comment