ጤና ይስጥልኝ ፡-
ግለሰቦች ከሕግ ወይም ከውል በመነጨ ግንኙነታቸው መካከል አለመግባባት ቢፈጠር ወይም የፍርድ ቤት ውሣኔ የሚያስፈልገው ጉዳይ ቢያጋጥማቸውና በዚሁ መሠረትም ፍ/ቤቱ ቢወስን ለውሣኔው ማስፈጸሚያ የሚሆን ንብረት ካለ ይህው ንብረት ተከብሮ የሚያዝና በፍርድ አፈጻጸም ምክንያት የሚወስድ ሲሆን ሆኖም ግን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 404 ተከብረው ስለማይያዙና በአፈጻጸም ወቅት ስለማይወሰዱ ንብረቶች እንመልከት፡-
መልካም ምንባብ፡-
- ለፍርድ ባለዕዳውና ለቤተሰቡ የዕለት አገልግሎት የሚጠቅሙ ልብሶች ፣ የምግብ ማብሰያ፣አልጋ፣
- ለዕለት ሙያ ሥራና ለንግድ ሥራ ማከናወኛ ተገቢ የሆነ ዕቃ፣
- የፍርድ ባለዕዳው ገበሬ ወይም በእርሻ ሥራ የሚተዳደር ከሆነ የዘር እሕልን ጨምሮ ለግብርና ሥራ አገልግሎት በቂ የሆነው፣
- ለራሱና ለቤተሰቡ ለሦስት ወራት መተዳደሪያ ገንዘብና ለዕለት ምግብ የሚሆን ፣
- ለጡረታ የሚከፈል ገንዘብ፣
- በባሕር ሕግ በቁጥር 121 የተመለከተው ድንጋጌ (የመርከበኛ ደመወዝ ከ1/4ኛ በላይ አይያዝም )
እንደተጠበቀ ሆኖ ከወር ደመወዝ ላይ ከ1/3ኛ በላይ ወይም በቀን ከሁለት ብር የማይበልጥ ሆኖ ሌላ ገቢ የሌለው እንደሆነ ፣
- በሕግ የተወሰነ እንደሆነ፣
- እንደዚሁም በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ሰሚው ችሎት የሰ/መ/ቁጥር 10489 እና 25019 በሆኑ አስገዳጅ ውሣኔዎች በበጀት የሚተዳደር የመንግስት መስሪያ ቤት የፍርድ ባለዕዳ ሆኖ ሲገኝ በበጀት የተያዘውን እና የሠራተኛ ደመወዝን የሚያካትተውን ገንዘብ ከባንክ ወጪ ሆኖ ለአፈጻጸም እንዲውል ማድረግ እንደማይቻልም ግንዛቤ እንያዝበት፡፡
መልካም ቀን
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!!!
ታህሳስ 13 2014ዓ.ም
ደረጀ ማርቆስ

Comments

Be the first to add a comment