👉የኳታሩ አል-ኻያት ቤተሰብ በ12.5 ቢሊዮን ዶላር በሚገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ላይ ለመሳተፍ ማቀዱ ተገለፀ!

በሶርያና ኳታር ውስጥ በጣም ትልቅና ሰፊ የንግድ ተቋም ያለው የአል-ኸያት ቤተሰብ በአፍሪካ መሰረተ-ልማት ላይ ኢንቨስት ለማድረግ እያቀደ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በ12.5 ቢሊዮን ዶላር በሚገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ፕሮጀክት ላይ ድርሻ ለመውሰድ ማለሙን ብሉምበርግ ዘግቧል።

የቤተሰቡ ንብረት የሆነው ዩሲሲ ሆልዲንግ የተሰኘው ኩባንያ በኢትዮጵያ ከሚገነባው ሜጋ አየር ማረፊያ በተጨማሪ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የ400 ኪሎ ሜትር አውራ ጎዳና ግንባታን ጨምሮ በአፍሪካ ትላልቅ የትራንስፖርት ፕሮጀክቶች ላይ ለመሳተፍ አልሟል።

ይህ ታዋቂ የባለሀብቶች ቤተሰብ በኅዳር 2025 ዓ.ም. በተካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የበዓለ-ሲመት ሥነ-ሥርዓት ላይ ከተገኙ ጥቂት ተደማጭ የዓለም ታዋቂ ሰዎች መካከል አንዱ ነበር።

ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምስራቅ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገነባውና በዛሃ ሃዲድ አርክቴክቶች ዲዛይን የተደረገው ይህ አዲስ አየር ማረፊያ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን የወደፊት የአቪዬሽን ማዕከልነት ለማጠናከር ያለመና በአፍሪካ ትልቁ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በዘንድሮው የጥር ወር ላይ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው የተጀመረውና 35 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሬት ላይ የሚያርፈው ይህ አውሮፕላን ማረፊያ፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ 60 ሚሊዮን ተሳፋሪዎችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት፣ አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ሲያልቅ በአመት እስከ 100 ሚሊዮን ተሳፋሪዎችን ማስተናገድ የሚችል የአህጉሪቱ ዋነኛ የትራንዚት መተላለፊያ ይሆናል።

@etconp

Comments

Be the first to add a comment