ሴቶችና ሕፃናት በአዲሱ የወንጀል ሥነ ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ
በ- ኃይሉ ሐሰና (ጠበቃ)
ባለፈው ዋስትናን በሁኔታ ስለ መከልከል በጻፍነው ላይ ሴቶችና ሕፃናት በአዲሱ የወንጀል ሥነ ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ ውስጥ ልዩ ትኩረት እንዳገኘ ገልጸን ነበር:: እስቲ ከመዘርዘር አንጻር ትንሽ ሰፋ አድርገን እንዳሠው:-

1. በሴቶችና ሕፃናት ላይ በተፈጸመ ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘን ሰው መርማሪ ፖሊስ በፖሊስ ዋስትና ሊፈታው አይችልም:: አንቀጽ 117(3)::

ማለትም ተጠርጣሪው ወንጀሉን ስለ መፈጸሙም ከነአካቴው ወንጀል ስለመፈጸሙ አጠራጣሪ ቢሆንም ስንኳ ለሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ትኩረት መስጠት ስለሚሻ ፖሊስ የግድ በፍ/ቤት የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ በማስከፈት የተጠርጣሪው የዋስትና ጉዳዩ በዳኛ እንዲታይ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

2. በሴቶችና ሕፃናት ላይ በተፈጸመ ወንጀል መጠርጠር/መከሰስ በራሱ በፍ/ቤት ዋስትና ለመከልከል በቂ ምክንያት ነው:: አንቀጽ 139(2/መ)

3. ፍርድ ቤቱ ዋስትና የፈቀደለት ሰው በሴቶችና ሕፃናት ላይ በተፈጸመ ወንጀል የተጠረጠረ ከሆነ ተጠርጣሪው በመልካም ባሕርይ ለመመራት የእጅ ጠብቅ ዋስ (guarantee of good conduct) እንዲገባ ቅድመ ሁኔታ ሊያደርግ ይችላል፡፡ 142(7)

4. ዐቃቤ ሕግ በሴቶችና ሕፃናት ላይ በተፈጸመ ወንጀል የወንጀል ክስ ሲያቀርብ በዚያው መዝገብ ዐብሮ ተከሳሽን ወክሎ የፍትሐብሔር (የካሳ) ክስ አጣምሮ የማቅረብ ግዴታ አለበት:: አንቀጽ 215(2)::

ስለሆነም የተደፈሩ፣ የተጠለፉ፣ ወይም ሌላ ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶችና ሕፃናት ካሳ ለመጠየቅ በራቸው በፍ/ብሔር ፍ/ቤት የዳኝነት ክፍያ ከፍለው ክስ እያቀረቡ መንከራተት አይኖርባቸውም::

5. ሴትን በመጥለፍ፣ አስገድዶ በመድፈር፣ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች እና መሰል በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በማድረግ በተከሰሱ ሰዎች ጉዳይ በባሕላዊ ሥርዓት አይታይም::

6. ለጥቃት የተጋለጠች ሴት/ሕፃን (የግል ተበዳይ) ምስክር ሲሆኑ የግድ በአካል በችሎት መቅረብ ሳይጠበቅባቸው የምስክርነት ቃላቸውን የሚሰጡበት ሁኔታ [VC, et.] ፍ/ቤቶች ሊያመቻቹ ይገባል: ተብሎ ተደንግጓል፡: አንቀጽ 21(6)

7. እንዲሁም የአስገድዶ መድፈር ወይም ጾታዊ ጥቃት የተፈጸመባት ሴት ወይም ሕፃን የምስክርነት ቃል በምትሰጥበት ጊዜ ዐብሯት ወላጆቿ (አሳዳሪዋ/ሞግዚቷ) እና የማኅበራዊና የሥነ ልቦና ድጋፍ የሚሰጥ ባለሙያ መገኘታቸውን ችሎቱ የማረጋገጥ አለበት:: አንቅጽ 79(3)(ለ)

8. ለመመስከር ያለመገደድ ልዩ መብት ሴቶችና ሕፃናትን አስመልክቶ ተፈጻሚ አይሆንም:: አንቀጽ 254
9. ይም የቤት ውስጥ ጥቃት በትዳር አጋር እና በወላጆችና በልጅ መካከል በሚፈጸምበት ጊዜ ምስክር ማግኘት አስቸጋሪ እንዳይሆን በሚል ነው፡፡
ስለሆነም ሚስት የባል-ሚስት፣ የልጅ-ወላጅ ለመመስከር ያለመገደድ ከለላን በማንሣት ምስክርነት መቃወም አይቻልም::👩🏽‍⚖️

10. የግል ተበዳይ የሆነች ሴት ወይም የሕፃን ወኪል ያቀረበችውን የግል አቤቱታ (complaint) ለማንሣት በፈለገች ጊዜ ፍ/ቤቱ ዐ/ሕግ አስተያየት እንዲሰጥ የማድረግ ግዴታ አለበት:: አንቀጽ 67/1/

እንደሚታወቀው በግል አቤቱታ ብቻ የሚያስቀጣ ወንጀል የተፈጸመበት የግል ተበዳይ ወይም ወኪሉ ከፍርድ ቤት በማንኛውም ጊዜ ያቀረበውን አቤቱታ በማንሣት በፍ/ቤት እየታየ ያለው መደበኛ ክስ እንዲቀር ማድረግ ይችላል::

ይሁንና በግል አቤቱታ ብቻ የሚያስቀጣው ወንጀል በሕፃናት እና ሴቶች ላይ የተፈጸመ ከሆነ ተጎጂዋ ሴት ወይም የሕጻኑ ወኪል ክሱን ለማንሣት ብትፈልግ/ቢፈልግ ፍ/ቤቱ ዐቃቤ ሕግ አስተያየት እንዲሰጥበት በማድረግ የግል ተበዳይ ወይም ወኪሉ አቤቱታውን ለማንሣት የወሰነው በነጻ ፈቃዱ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት::

ስለሆነም ዐቃቤ ሕግ የግል አቤቱታውን መነሣት ከተቃወመ ወይም የግል አቤቱታውን ለማንሣት የወሰነችው ጥቃትን በመፍራት እንደሆነ ካረጋገጠ ፍ/ቤቱ የግል አቤቱታ ለማንሣት የቀረበውን ማመልከቻ ውድቅ በማድረግ ክሱ መታየቱ እንዲቀጥል ያዛል::🧑🏾‍⚖️

11. በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የወንጀል ምርመራና ክስ አመሠራረትን በተመለከተ ፍትሕ ሚኒስቴር ልዩ መመሪያ ያወጣል፡፡ 430(3/ቸ)

*እንግዲህ በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ መርማሪ ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ ፍትሕ ሚ/ር የሚያወጣውን ልዩ መመሪያ ተከትለው የመሥራት ግዴታ ይኖርባቸዋል::👴🏽🧓🏾

——— ——— ——— ———
ምንጭ:-ከጠበቃ ሃይሉ ሃሰና

ማህበራዊ ሚዲያ የተወሰደ

Comments

Be the first to add a comment