የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
በሕግ አስከባሪ አካላት ያለአግባብ ጉዳት የደረሰበት ሰው ምን መፍትሔ አለው? /የሕግ ጉዳይ/
አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ሹም (ፖሊስን ይጨምራል) የሥራ ጥፋት ፈጽሞ በሰው ላይ ጉዳት ካደረሰ መንግሥት ካሳ የመክፈል ግዴታ አለበት።(የፍሕቁ 2126 /2/)። ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ሹም የሚፈጽመው ጥፋት ደግሞ የሥራ ጥፋት ነው ተብሎ ይገመታል።(የፍሕቁ 2127 /3/)። ስለዚህ ፖሊስ ወንጀል ለመፈጸሙ ምክንያታዊ ጥርጣሬ ሳይኖረው ሰው ቢይዝ፣ ፍርድ ቤት ሳይፈቅድለት ከ48 ሰዓት በላይ ሰው በእስር ቢያቆይ፣ ወይም በእስረኞች ላይ ድብደባ ቢፈጽም የሥራ ጥፋት ነው ማለት ነው። ለዚህ የፖሊስ ጥፋት መንግሥት ማለትም የፖሊስ ተቋም ፍትሐብሔራዊ ሀላፊነት ይኖርበታል ማለት ነው። ለተጎጂዎች ካሳ ለመክፈል ይገደዳል። ይህ በተግባር ሲሠራበት ባይታይም ሕጉ የሚለው ይህንን ነው።
በተመሳሳይ ዐቃቤ ሕግም ማስረጃ ወይም ሕግ ሳይኖር ሰው ያለአግባብ ቢከስ የሥራ ጥፋት ነው። ስለዚህ መሥሪያ ቤቱ ካሳ ለመክፈል ይገደዳል። ነገርግን ፖሊስ ካሰባሰበው ማስረጃ አንጻር ዐቃቤሕግ በበቂ ምክንያት ከከሰሰ እና ተከሳሹ ተከላክሎ ቢወጣ በፖሊስም ሆነ ዐቃቤ ሕግ በኩል የተፈጸመ ሙያዊ ጥፋት አለ ለማለት አይቻልም። በተግባር ብዙም ባይሠራበትም ሕጉ ይሄው ነው።
ሌላው ሠራተኛው ወይም ሹሙ የሥራ ሳይሆን የግል ጥፋት የፈጸመ እንደሆነ በፍሕቁ 2126 /3/ መሠረት መንግሥት ከሀላፊነት ነጻ ቢሆንም ሹሙ ወይም ሠራተኛው ግን ለግል ጥፋቱ ከመጠየቅ ከለላ የሚሰጠው ሕግ የለም። ስለዚህ አንደኛ ነገር ሁልጊዜ የተፈጸመው ጥፋት የሥራ ጥፋት ነው ተብሎ ይገመታል። ሁለተኛ ነገር ለተፈጸመው የሥራ ጥፋት መንግሥት ካሳ ይከፍላል። ሦስተኛ ጥፋቱ የሹሙ ወይም የሠራተኛው የግል ጥፋት ሆኖ ቢገኝ እንኳን በግሉ ከመጠየቅ አያመልጥም። በእርግጥ መንግሥት ካሣ የከፈለ እንደሆነ የከፈለውን ካሳ ጥፋቱን ከፈጸመው ፖሊስ ወይም ዐቃቤ ሕግ በግል የመጠየቅ መብት አለው።
አሁን ይሄ በፖሊስና ዐቃቤ ሕግ ላይ ሲተገበር አይሰተዋልም እንጂ ቢተገበር ምን ይጎድለዋል ?
በአጠቃላይ በፖሊስ ወይም በዐቃቤ ሕግ ለሚፈጸሙ ጥፋቶች ጉዳት ካሳ ለመጠየቅና መልካም ስም እንዲሁም የተያዘ ንብረት ለማስመለስ የሚያስችል በቂ ሕግ አለን። የሚያስፈልገው መተግበርና መብትን መጠየቅ ብቻ ነው። ግለሰቦች መብታቸውን በመጠየቃቸው በግል ተጠቂ የማይሆኑበትን ሁኔታ ማመቻቸት ላይ ይበልጥ ቢሠራ የተሻለ ነው። የካሳ ሕጉን የፖሊስና ዐቃቤ ሕግ ተጎጂዎች እንዴት ውጤታማ በሆነ መንገድ ሊጠቀሙበት ይችላል በሚለው ላይ ጥናቶችና ውይይቶች ቢደረጉ ውጤታማ ነው።#Tamerat kidanemariam
Comments
Be the first to add a comment