ጤና ይስጥልኝ
ባለፈው ጽሑፋችን የምርጫ ማስፈጸሚያ አደረጃጀቶችን የተመለከትን ሲሆን በዚህ ጽሑፍ ስለምርጫ አፈጻጸም የምናቀርብ ይሆናል፤
መልካም ንባብ!
ስለምርጫ አፈጻጸም በምንመለከት ጊዜ መራጭ እና ተመራጭ መኖራቸው የግድ የሚልና ለመራጭነትም ሆነ ለተመራጭነት ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆንና ለዚሁ ሲባል በተዘጋጀ ሰነድ ላይ የመመዝገብና በሕግ ክልከላ ያልተደረገበት መሆን የሚያስፈልግና ለመራጭነት ዕድሜ 18 ዓመት ለተመራጭነት ዕድሜ 21 ዓመት በምዝገባ ዕለት የሞላው መሆን ግድ ይላል፡፡
የምዝገባ ቦታ ለመራጮች በምርጫ ጣቢያ ሲሆን ለተመራጮች በምርጫ ክልል ሆኖ ቦርዱ በሚወስነው መሠረት የምዝገባ የጊዜ ስሌዳ የሚበጅለትና በተለይ ተመራጮች በዕጩነት ለመመዝገብ በሕግ ላይ የተቀመጠውን በተለይም የድጋፍ ፊርማንና የመሳሰሉትን መስፈርት በሟሟላት መሆን ይገባዋል፡፡ሆኖም አንድ ዕጩ ቢሞት ሊከናወን ስለሚገባው ሥነ-ሥርዓት ለዚሁ ሲባል ከወጣው አ/ቁጥር 1162/2011 መመልከት እንደሚቻል እናስታውሳለን፡፡
ለምርጫ የተመዘገቡ ዕጩዎች ምርጫው እስኪጠናቀቅ ድረሰ እጅ ከፍንጅ ካልተያዙ በስተቀር በወንጀል ተጠርጥረው እንደማይያዙ የተገለጸ ሲሆን ዕጩ ተወዳዳሪዎች ቦርዱ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ሕግ የጣለውን ግዴታ በማክበርና ቦርዱ በሚያወጣው የሥነ-ምግባር ደንብ መሠረት በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉትን መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻን ከተከለከለባቸው ቦታዎች ውጪ የሚያደርጉ ሲሆን ከዚህ በኋላ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የድምፅ መስጠቱ ሥርዓት በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 54/1 መሠረት ነፃ፣ቀጥተኛ ና ትክክለኛ በሆነና በሚስጥር ድምፅ የሚሰጥና ቦርዱ በሚወስነው ቀን መሠረት አንድ ላይ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የሚሰጥና የድምፅ ቆጠራ ድምፅ በሚሰጥበት ምርጫ ጣቢያ ተደርጎ ከምርጫው ቀን ቀጥሎ ባሉት 10(አስር) ቀናት ውስጥ ውጤቱ የሚገለጽ ሲሆን በድምፅ አሰጣጥ ወቅት ያሉትን ዝርዝር ጉዳዮችን በአዋጁ ላይ እንድትመለከቱ በመጋበዝ ጽሑፉን ቋጨን፡፡
መልካም ዕለት!
ደረጀ ማርቆስ
ሕዳር 2013 ዓ.ም

Comments

Be the first to add a comment