የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሕገመንግስቱ እና በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 10
መሠረት የተሰጠው ስልጣን በአዋጁ በዝርዝር በተመለከቱት እና መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስሕተት የተፈጸመበትን የመጨረሻ ውሳኔ ማረም
ነው፡፡ ይህን ስልጣኑን መሠረት በማድረግ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በበርካታ ጉዳዮች ላይ የሕግ ትርጉም ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በዚህም በአገሪቱ
ውስጥ ወጥ የሆነ የሕግ አረዳደር እና አተርጓጎም እንዲኖር በማድረግ ሕገመንግስታዊ ግድታውን ሲወጣ ቆይቷል፡ በሰበር ሰሚ ችሎቱ
ከአምስት ባላነሱ ዳኞች የተሰጠ የሕግ ትርጉም ውሳኔው ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ በየትኛውም ደረጃ በሚገኝ የፌዴራልም ሆነ የክልል ፍርድ
ቤት አስገዳጅነት ይኖረዋል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 26(1)እና(4) ላይ እንደተገለጸው አምስት ዳኞች የተሰየሙት የሰበር ሰሚ ችሎት
በባለጉዳዮቹ አመልካችነት ወይም በችሎቱ በራሱ አነሳሽነት ቀድሞ የተሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በተለያዩ ምክንያቶች ማሻሻል
አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ከሰባት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ሰሚ ችሎት እንዲታይ በቂ እና አሳማኝ ምክንያቶችን ተንትኖ በመግለጽ
ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል፡፡ በዚህ አግባብ በሰባት ዳኞች የተሰጠው ውሳኔም ውሳኔው ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ
አስገዳጅ ነው፤ በዚህ አግባብ መሠረት ከሰባት ያላነሱ ዳኞች የተሰየሙበት የሰበር ችሎት ቀድሞ የሰጠውን የሕግ ትርጉም ከሰባት ባላነሱ
ዳኞች በተመሳሳይ ጭብጥ በሌላ ጊዜ ሊሻሻል ይችላል በማለት የደነግጋል፡፡ ( አስቀድሞ የተሰጠው ውሳኔ በሰባት ዳኛ ሊለወጥ ይገባል
ወይስ አይገባል ለማለት የሚያስችሉ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው የሚለወ በአዋጁ ላይ አመላካች ነገር እንዳልተቀመጠ ልብ ይሏል )
ሰበር ሰሚ ችሎቱ በተለያዬ ጊዜ የውርስ ይርጋን አስመለክቶ የሰጣቸው ውሳኔዎች እርስ በእርስ ያላቸው መስተጋብር ምንድነው የሚለውን
ለመለየት ውሳኔዎቹን በአግባቡ ማየት ይጠይቃል፡፡ በዚህ ዓመት በሰባት ዳኞች በሰ.መ.ቁ 243973 ጥቅምት 06 ቀን 2017 ዓ.ም
የተሰጠው ውሳኔም በአግባቡ ሊታይ የሚገባው ሌላው ውሳኔ ነው፡፡ በሰባት ዳኞች ታይቶ የውርስ ንብረት ክፍፍልን
አስመልክቶ ቀደም ሲል ተይዞ የነበረውን አቋም በመቀየር ውሳኔ ሲሰጥ ከውሳኔው ሰጪ ዳኞች አንዷ ነበርኩ፡፡ ይህ ውሳኔ
በሌላ ሰባት ዳኞች ታይቶ ሊለወጥ ይገባል ወይስ አይገባም ለማለት በተጨባጭ በማሕበረሰቡ ዘንድ ያለውን የኑሮ መስተጋብር
እና እያመጣ ያለውን ውጤት በአግባቡ ማጤን ይፈልጋል፡፡ ቀደም ሲል ሰበር ሰሚ ችሎቱ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1000 መሠረት
በተለያዩ መዛግብት ላይ የሰጣቸውን ውሳኔዎች እና በሰባት ዳኞች ታይቶ የተሰጠው ውሳኔ አጭር ማጠቃለያ እንደሚከተለው
ቀርቧል፡፡
➢ በመሠረቱ ይርጋ መብቱ ወይም ጥቅሙ የተነካበት ሰው በሌላ ሰው ላይ የሚያቀርበውን ክስ፤ አቤቱታ ወይም የይገባኛል ጥያቄ
አስመልክቶ በሕግ ተለይቶ የተቀመጠ የክስ ማቅረቢያ ጊዜ ነው፡፡ የይርጋ ጽንሰ ሐሳብ ሶስት መሠረታዊ ምክንያቶችን የያዘ
ነው፡፡ እነኚህም፡-
1. ከሳሽ በተገቢው ትጋት እና በቂ ምክንያት መብቱን እንዲጠይቅ ማስቻል እና ዳተኛ የሆነ ተከራካሪ ወገን እንዳይኖር
ማድረግ፤
2. ተከሳሽ በጣም ዘግይተው የሚመጡ ክሶችን ለመከላከል የሚያስችሉትን ማስረጃዎች እንዳያጣ ማድረግ፤
3. ዘግይው የሚቀርቡ ክሶች ዓላማቸው ፍትሕ ከማስገኘት ይልቅ ለበቀል እና ለማጥቂያ እንዳይውሉ ማድረግ ናቸው
የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1000(1) ድንጋጌ ከሳሹ መብቱን እና የውርስ ንብረቶች በተከሳሹ መያዛቸውን ካወቀ ሶስት ዓመት ካለፈ በኋላ ስለ ወራሽነት
ጥያቄ የሚቀርበው ክስ ተቀባይነት ለማግኘት አይችልም በማለት ይደነግጋል፡፡ የዚሁ ሕግ ንዑስ (2) ድንጋጌ ደግሞ እንደዚሁም ሟቹ
ከሞተበት ወይም በመብቱ ለመሥራት ከቻለበት ቀን አንስቶ አስራ አምስት ዓመት ካለፈ በኋላ ከዘር የወረደ ርስት ካልሆነ በቀር የተባለው
የውርስ ጥያቄ ክስ በማናቸውም አስተያየት ቢሆን ተቀባይነት ማግኘት አይችልም በማለት ይደነግጋል፡፡

Comments

Be the first to add a comment