የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
ስለንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ሕግ (ክፍል ሁለት)
የነጋዴ ግዴታዎች
ሸማቾች ያላቸውን መብት ከላይ ከተዘረዘሩት መብቶቻቸው በተጨማሪም የነጋዴዎች ግዴታ ለሸማቾች መብት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ነጋዴዎች በርካታ ግዴታዎች ያሉባቸው ቢሆንም በዋናነት ግን፡- የዋጋ ዝርዝር በንግድ ቤቱ ላይ መለጠፍ፣ የንግድ ዕቃዎች ላይ መግለጫ መለጠፍ፣ ደረሰኞችን መስጠትና ቀሪዎችን መያዝ፣ የራሱን /የንግድ ስሙን/ ስለመግለጽ፣ የንግድ ማስታወቂያ ትክክለኛ መሆን ወዘተ የሚሉ ግዴታዎች አሉባቸው፡፡ (ከአንቀጽ 15-18)
ጉድለቶችን እና የተከለከሉ ድርጊቶችን በተመለከተ
ሸማች በገዛው የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ላይ ያገኛቸውን ጉድለቶችና ጉድለቶቹ ሊያስከትሉ ስለሚችሉት ጉዳት ለሚኒስቴሩ ወይም ለሚመለከተው ቢሮ ማሳወቅ ይችላል፡፡ ለሸማቹ የበለጠ የሚጠቅሙ ዋስትናዎች ወይም የሕግ ወይም የውል ድንጋጌዎች በነጋዴው ሊቀርብለት ይችላል፡፡ ሆኖም ሸማቹ ጉድለት ያለበት የንግድ ዕቃን የሚመለከት ሲሆን የንግድ ዕቃው እንዲለወጥለት ወይም ዋጋው እንዲመለስለት ሻጩን መጠየቅ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ጉድለት ያለበት አገልግሎት ሲሆን አገልግሎቱ በድጋሜ ያለክፍያ እንዲሰጠው ወይም የአገልግሎት ክፍያው እንዲመለስለት ሻጩን መጠየቅ ይችላል፡፡ ግዥው በተፈጸመ በ15 ቀናት ውስጥ ሻጩን መጠየቅ የሚችል መሆኑን ከአዋጁ እንረዳለን፡፡
ሸማቹ በሕጉ የተሰጡትን መብቶች የሚያስቀሩ በሸማችና በነጋዴ መካከል የሚደረጉ የውል ግዴታዎች ተፈጻሚነት አይኖራቸውም::
ለማንኛውም ነጋዴ የሚከተሉትን ድርጊቶች መፈጸም የተከለከለ ነው፡- በአጠቃላይ ስለንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች የተሳሳተ መረጃ መስጠት፤ የንግድ ዕቃዎችን ሞዴል፣ አዲስ የተሠሩ፣ የተለወጡ፣ እንደገና እንደ አዲስ የተሠሩ ወይም ያገለገሉ ስለመሆናቸው ወይም በአምራቹ እንዲሰበሰቡ የተባሉ ስለመሆናቸው በትክክል አለመግለጽ፤ የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶችን በማስታወቂያ እንደተነገረላቸው አለመሸጥ ወይም ማስታወቂያው የመጠን ውስንነት መኖሩን ካልገለፀ በስተቀር ሸማቾች በሚፈልጉት መጠን ልክ አለመሸጥ፤ ከንግድ ዕቃ ወይም ከአገልግሎት ሽያጭ ጋር በተያያዘ የተገባ የዋስትና ግዴታን አለመወጣት፤ የንግድ ዕቃ የሚያስፈልገው ጥገና ግዴታን አለመወጣት፤ የንግድ ዕቃ የሚያስፈልገው ጥገና ወይም የሚተኩ ክፍሎቹ እንደማያስፈልጉት አድርጎ ማቅረብ፤ ማንኛውም አገልግሎት የመስጠት ሥራን በንግድ ሥራው ከሚታወቀው ደረጃ በታች ወይም ባልተሟላ ሁኔታ መስጠት፤ ለሰው ጤናና ደህንነት አደገኛ የሆነ፣ ምንጩ ያልታወቀ፣ የጥራት ደረጃው የወረደ፣ የተመረዘ፣ የአገልግሎት ጊዜው ያለፈ ወይም ከባዕድ ነገሮች ጋር የተደባለቀ የንግድ ዕቃን ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ፤ በንግድ ዕቃ ወይም የአገልግሎት ግብይት ማንኛውንም የማጭበርበር ወይም የማደናገር ተግባር መፈፀም፤ የሸማቹን መብት ለመጠበቅ ሲባል ካልሆነ በስተቀር የንግድ ዕቃን ወይም አገልግሎትን አልሸጥም ማለት፤ የደረጃዎች ማህተም መጠቀም የሚያስፈልጋቸው የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ያለደረጃ ማህተም ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ፤ የንግድ ዕቃን ወይም አገልግሎትን በንግድ ዕቃው ላይ ወይም በንግድ መደብሩ ውስጥ ከተለጠፈው ዋጋ አስበልጦ መሸጥ፤ የንግድ ዕቃዎች የተሰሩበትን አገር አሳስቶ መግለጽ፤ በሸማቾች መካከል ተገቢ ያልሆነ አድልዎ መፈጸም፤ አንድን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ለመሸጥ ሸማቹ ያልፈለገውን ሌላ የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት አብሮ እንዲገዛ ማስገደድ፤ ሕገ-ወጥ በሆነ ማንኛውም የመለኪያ መሳሪያ መጠቀም እና የመሳሰሉት የተከለከሉ ናቸው፡፡
ቸር ሰንበቱ!!
ፌናን ተጊበሉ
የካቲት 16/2013 ዓ.ም
Comments
Be the first to add a comment