የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በዛሬው እለት ከቀብር ስነስርዓትና አስክሬን ምርመራ፣ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ እና የቤት ውስጥ ራስን ለይቶ ማቆየትን በተመለከተ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ይፋ አድርገዋል።

በዚህ መሰረት በተለያዩ ምክንያቶች ለሞት የሚዳረጉ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በማህበረሰቡ የቀብር ሥነ-ሥርዓት መፈጸም ተፈቅዷል። ይህም ከዚህ ቀደም የአስክሬን የላብራቶሪ ውጤት ከመምጣቱ በፊት የቀብር ሥነ-ሥርዓት መፈጸም አይቻልም የሚለውን መመሪያ መሻሻሉን ዶክተር ሊያ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ በቀብር ሥፍራ ላይ ከዚህ ቀደም የተቀመጠው 50 ሰዎች ብቻ ተገኝተው ሥርዓቱን ማከሄድ አለባቸው የሚለው መመሪያው አልተሻሻለም።

ግለሰቦች በኮሮናቫይረስ ቢያዙ የሚያገለግሏቸው የቤተሰብ አባላትና የራሳቸው ፍላጎት ከግምት በማስገባት ተፈጻሚ የሚሆን መሆኑንም ጠቅሰዋል። የግለሰቦችን የአኗኗር ሁኔታ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት አግባብ ከሆነ በቤታቸው እንዲቆዩ እንደሚደረጉም ተገልጿል።

ከውጭ የሚገቡ ሰዎች በተለይም ወደ አገር ከገቡ በኋላ ባለፉት ሦስት ቀናት ውስጥ ከመጡበት አገር ተመርምረው ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ መረጃ ይዘው ከመጡ ናሙና ተወስዶ በቤታቸወ 14 ቀናት እንዲቆዩ ይደረጋልም ተብሏል።

በሌላ በኩል ነጻ መሆናቸውን የሚያረጋገጥ ሪፖርት ይዘው ለማይመጡ መንገደኞች ናሙናቸው ተወስዶ ለሰባት ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ ይደረጋል ብለዋል። ይህም ከዚህ ቀደም ለ14 ቀናት የነበረውን አስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ወደ ለ7 ቀናት ብቻ እንዲሆን ተወስኗል።
@tenaet

Comments

Be the first to add a comment