ህገ-ወጥ የስራ ውል መቋረጥ የሚያስከትለው ውጤት

የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ለተዋዋይ ወገኞች ፈቃድ ብቻ እንዳይተውና ህግ ጣልቃ እንዲገባ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ ከስራ ውል መቋረጥ ጋር የተያያዘ ምክንያት ነው፡፡  ስለዚህም የስራ ውል በዘፈቀደ ሳይሆን በበቂ ምክንያቶች ላይ ተመስርቶ የተቋረጠ መሆኑን ለማረጋገጥ ሕግ አስፈላጊውን ጥበቃ ያደርጋል፡፡ በአሰሪና ሰራተኛ መካከል ያለ የስራ ውል በአሰሪው አነሳሽነት፣በሠራተኛው አነሳሽነት፣በህግ በተደነገገው መሰረት እና በህብረት ስምምነት በተቀመጠው መሰረት ሊቋረጥ የሚችል ሲሆን በህግ ተቀባይነት ያለው የስራ ውል መቋረጥ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ከአንቀፅ 23 ጀምሮ እና ዝርዝር ምክንያቶቻቸውና ሁኔታዎቻቸው ደግሞ ከዚሁ አንቀጽ ቀጥለው በሚገኙት አንቀጾች ተደንግገዋል፡፡

•  በአሰሪው አነሳሽነት የሚደረግ የስራ ውል መቋረጥ እንደየ ሁኔታው በማስጠንቀቂያ ወይም ያለማሰጠንቀቂያ ሊደረግ የሚችል ሆኖ የምክንያቶቹ ዝርዝር እና አፈጻጸሙ ከአንቀጽ 26 እስከ 30 ተደንግገው ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በሕብረት ስምምነት መሰረት ያለማስጠንቀቂያ ውሉን ለማቋረጥ የሚያበቃ ምክንያት ተደርጎ የተወሰደ ጉዳይም በአሰሪው አነሳሽነት ያለማስጠንቀቂያ ውሉን ሊያቋርጥ የሚችል መሆኑ በአንቀጽ 27/1/ተ/ ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡  የስራ ውል በአሰሪው አነሳሽነት ሊቋረጥ የሚችለው የሰራተኛውን ጠባይ ወይም የሰራተኛው የመስራት ችሎታን ከሚመለከቱ ግልጽ ሁኔታዎች ወይም ከድርጅቱ ድርጅታዊ አቋም ወይም የስራ እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት ባላቸው ምክንያቶች ብቻ ነው፡፡

•  በሰራተኛው አነሳሽነት የሚደረጉት ደግሞ ልክ በአሰሪው አነሳሽነት ሊደረግ እንደሚችለው በማስጠንቀቂያ እና ያለማሰጠንቀቂያ ውሉን የሚያቋርጥበት መንገድ  ሲሆን ( ለምሳሌ የስራ ውልን ያለማስጠንቀቂያ ማቋረጥ ከሚቻልባቸው ምክንያቶች ውስጥ  አሰሪው የሰራተኛውን ክብርና ሞራል የሚነካ ወይም በወንጀል የሚያስቀጣ ሌላ አድራጎት የፈፀመበት እንደሆነ) ሁኔታዎቹና ምክንያቶቹ ከአንቀጽ 31 እስከ 33 ተደንግነው ይገኛሉ፡፡


•  ውሉ በሕግ የሚቋረጥበት ምክንያቶች በአብዛኛው ከሁለቱም ወገን ቁጥጥር ውጭ ያሉ ሲሆን( የሰራተኛው መሞት፣በጡረታ መገለል፣የድርጅቱ መክሰር ወይም መዘጋት ወ.ዘ.ተ  አንቀጽ 24)፤ የስራ ውል ሁለቱም በፈቃደኝነት የሚገቡበት እንደመሆኑ ሁሉ ሁለቱም በፈቃኛነት ከተስማሙ ውሉን ሊያቋርጡ የሚችሉበት ሁኔታም በአንቀጽ 25 ስር ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ከላይ በተገለጹት ቁጥሮች በተደነገጉት ምክንያቶችና ሁኔታዎች የሚፈጸም የስራ ውል መቋረጥ ሕጋዊ የስራ ውል መቋረጥ ሲሆን ከነዚህ ውጭ የሚደረጉ የስራ ውል መቋረጥ በሕገወጥነት የሚፈረጁ ናቸው (አንቀጽ 42 ድረስ በዝርዝር ተቀምጧል)፡፡

ሰራተኛው የስራ ውሉን በህገ ወጥ መንገድ ሲያቋርጥ የሚያስከትለው ውጤት
በሠራተኛው አነሳሽነት የሚፈጸም የስራ ውል መቋረጥ ሕገወጥ ሊሆን የሚችለው ሠራተኛው ያለማስጠንቀቂያ ማቋረጥ ከሚችልባቸው በአንቀጽ 32 ስር ከተደነገጉት ውጪ ባሉ ሌሎች ምክንያቶች ሆኖ ነገር ግን ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ማስጠንቀቂያ ለአሰሪው ሳይሰጥ ውሉን ያቋረጠ ከሆነ ነው፡፡ በዚህ መልኩ የስራ ውሉን ያቋረጠ ሠራተኛ ለአሰሪው አሰሪው ለሱ ከሚከፍለው ቀሪ ክፍያ ውስጥ ከሠላሳ ቀናት ያልበለጠ ክፍያን በካሳ መልክ መክፈል ይኖርበታል (አንቀጽ 45)፡፡

አሰሪው የስራ ውሉን በህገ ወጥ መንገድ ሲያቋርጥ የሚያስከትለው ውጤት
አንድ አሰሪ ሰራተኛውን በህገ-ወጥ መንገድ ከስራ ቢያሰናብት ሰራተኛው ሊያገኛቸው የሚችላቸው መፍትሔዎች ምንድናቸው ወይም ውጤቱ ምን ይሆናል ለሚለው በአዋጁ ክፍል 4 አንቀፅ 43 መሰረት እንደ ጉዳዩ ሁኔታ ሠራተኛው ወደ ስራ እንዲመለስ አልያም የስራ ስንብት ክፍያን ጨምሮ ካሳ እና ሌሎች ተያያዥ ክፍያዎች ተከፍለውት የስራ ውል መቋረጡ እንዲፀና ሊደረግ ይችላል፡፡ የሰራተኛው ወደ ስራ መመለስ የስራ ከባቢውን የሚረብሽ ከሆነ እና በአሰራው እና በሰራተኛው መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሻክር ከሆነ ወደ ስራ ከመመለስ ይልቅ በህጉ የተቀመጡትን ክፍያዎች ፈፅሞ ማሰናበት የተሻለ አማራጭ በመሆኑ ህጉ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ሁለቱን አማራጮች ያስቀመጠ ሲሆን ይህንንም በማጠናከር የፌ/ጠ/ፍ/ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 18581 ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡

Comments

Be the first to add a comment