👉የካሳ ክፍያን በተመለከተ የክልል እና የፌደራል መንግስት እርስ በእርሳቸው ‛ማን ይክፈል’ á‰ áˆšáˆˆá‹ ባለመስማማታቸው áŠŤáˆł ሊከፈላቸው የሚገባቸው አካላት እየተንገላቱ መሆኑ ተገለጸ

🚧ለልማት ሲባል በሃይል የሚነሱ ዜጎች የሚገባቸውን ካሳ እንደማይከፈላቸው የገለጸው የኢትዮጵያ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ለዚህ ችግር አስፈፃሚ አካላት ህግን ተከተለው ባለመስራታቸው፣ የክልል እና የፌደራል መንግስት እርስ በእርሳቸው “አንተ ክፈል አንተ ክፈል” በመባባል ላይ እንደሆኑ አስታወቀ።

በቅርቡ የወጣው የካሳ አዋጅ ክልሎች እንዲከፍሉ የሚደነግግ ሲሆን ከዚህ ቀደም ያለው ደግሞ የፌደራሉ እንዲከፍል የሚያዝ ነበር።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የ2018 በጀት ዓመት የ11 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት አቅርቧል።

ተቋሙ በሪፖርቱ ላይ ባለፉት ወራት የደረሱትን በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የአስተዳደር በደል አቤቱታዎችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል።

አክሎም ለተለያዩ የልማት ሥራዎች ሲባል ዜጎችን በኃይል የማንሳትና ተገቢውን ካሳ ያለመስጠት ድርጊት አሁንም አሳሳቢ ሆኖ የቀጠለ ድርጊት ነው áˆ›áˆˆá‰ąáŠ• ለምክር ቤቱ  ካዘጋጀው ሪፖርት አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

ዕንባ ጠባቂ ተቋም አክሎም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና የንብረት ካሳ የሚከፈልበት ሁኔታን አስመልክቶ አድርጌዋለሁ ባለው ስልታዊ ምርመራና መደበኛ ቁጥጥር በአስፈጻሚ አካላት በኩል ሰፊ የሕግ ጥሰት አለ ሲል ይፋ አድርጓል።

ተቋሙ በግኝቱ ላይ እንዳመለከተው፣ በአዋጁ ላይ በግልጽ የተቀመጠ ድንጋጌ በቀጥታ እየተጣሰ ይገኛል።

በመሠረተ ልማት ግንባታ ምክንያት የሚነሱ ዜጎች ከመነሳታቸው ቢያንስ አንድ ዓመት በፊት ሾለ ልማቱ ዓይነት፣ ጠቀሜታና አጠቃላይ ሂደት እንዲያውቁት  አይደረግም ብሏል።

ከዚህም በላይ በቦታው ላይ ከሚገኙ ተነሺዎች የንብረት ልኬትና መጠን መረጃ ሳይሰበሰብና ሊከፈላቸው የሚገባው የካሳ መጠን ሳይወሰን ዜጎች “በኃይል” ከይዞታቸው እንዲነሱ እየተደረገ መሆኑን ተቋሙ አረጋግጫለሁ ብሏል።

በዚህም ምክንያት ባለመብቶቹ መሬታቸውን በኃይል ከተቀሙ በኋላ መብታቸውን ለማስከበር በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ደጃፍ ለአቤቱታ ለመንከራተትና ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸውን ገልጿል።

ሌላው የዕንባ ጠባቂ ተቋሙ  በሪፖርቱ ላይ የጠቀሰው ትልቅ ክፍተት፣ ካሳ ከተወሰነ በኋላም ለመክፈል ረዥም ጊዜ የሚወስድ መሆኑና አንዳንዶቹ ጉዳዮች ዓመታትን ማስቆጠራቸውን የተመለከተው ነው።

በተጨማሪም በ2016 በወጣው አዋጅ  ላይ ባለው የግልጽነት መጓደል ምክንያት የክፍያ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ክልሎች ወደ ፌደራል፣ ፌደራል ደግሞ “የክልሎች ሥልጣን ነው” በሚል ኃላፊነትን እርስ በርስ በመገፋፋት በባለጉዳዮች ላይ መጉላላት እየፈጠሩ መሆኑን አንስቷል።

ተቋሙ ለማሳያ እንዲሆን አድርጌዋለሁ ባለው የቁጥጥር ስራ በአማራ ክልል የሚገኘው የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ለልማት ተነሺዎች በሕግ ከተደነገገው በተቃራኒ 141.3 ሚሊዮን ብር ለአረጋውያንና ለአካል ጉዳተኞች የሚገባውን ካሳ ሳይከፍል ቆይቷል ብሏል።

ተቋሙ ባለፉት 11 ወራት ውስጥ 1,715 የአስተዳደር በደል አቤቱታዎችን ተቀብሎ መመርመሩን አስታውቋል።

በእነዚህ መዝገቦች ላይ በተደረገው ማጣራትና ምርመራ በአጠቃላይ 44,901 ዜጎች “የአስተዳደር በደል ደርሶብናል” በማለት ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

ከአቤቱታ አቅራቢዎቹ መካከል 17,002 ወንዶች ፤7,934 ሴቶች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ 19,965 ደግሞ በቡድንና በሌላ መልክ የቀረቡ በመሆናቸው በፆታ ያልተለዩ መሆናቸውን ሪፖርቱ ያሳያል።

አቤቱታዎች ከቀረቡባቸው ዋና ዋና ዘርፎች መካከል 452 ጉዳዮች የአገልግሎት ዕጥረት፣ የ408 መሬት ይዞታ ክርክር፣ 306 የሥራ ቅሬታዎች እንዲሁም 197ቱ የካሳ ክፍያነ የተመለከቱ ናቸው።

ተቋሙ ወስጃዋለሁ ባለው የማስተካከያ እርምጃ እና  በሰጣቸው የመፍትሔ ሐሳቦች አማካይነት 82 ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን፣ 1,319 ሠራተኞች ደግሞ የደረጃ ዕድገትና ዝውውር መብታቸው ተከብሮላቸዋል ሲል አስታውቋል።

በተጨማሪም ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ የደመወዝና ጥቅማጥቅም ውዝፍ ክፍያ ለባለጉዳዮች እንዲሰጥ የተደረገ ሲሆን፣ 41 አቤቱታ አቅራቢዎች ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙና በአጠቃላይ 36,200 ካሬ ሜትር ምትክ ቦታ ለተነሺዎች እንዲሰጥ ተደርጓል ብሏል።

የዕንባ ጠባቂ ተቋሙ የምርመራ ሥራ ማካሄድ ብቻውን በቂ አለመሆኑን በመጥቀስ፣ የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ጥብቅ የክትትል ሥራ እየተከናወነ ቢሆንም አንዳንድ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ለተቋሙ ሥራ ፈቃደኛ አለመሆንና የሚሰጡ ምክረ ሐሳቦችን በተገቢው ፍጥነት አለመፈጸም እንደ ትልቅ ማነቆ ሆኖብኛል ብሏል።

በቀጣይ ለልማት የሚነሱ ዜጎች ሰብዓዊና አስተዳደራዊ መብቶች አስቀድመው እንዲከበሩና የመንግስት አስፈጻሚ አካላት ለሕግ ተገዥ እንዲሆኑ ምክር ቤቱ የበኩልን ድርሻ እንዲወጣ እና እንድከታተል ጥሪ አቅርቧል።

Via Addis Maleda

@etconp

Comments

Be the first to add a comment