የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
ቅምሻ ስለሕገመንግስቱ፡-
ጤና ይስጥልኝ!
ባለ 11 ምዕራፍና ባለ 106 አንቀጹ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመንግስት የሀገሪቱ የህጎች ሁሉ የበላይና የስልጣንም ምንጭ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡
በዚች መልዕክት በፓርላመንታዊው መንግስት የፕሬዝንዳንትና የጠቅላይ ሚንስትሩን ስልጣንና ሀላፊነት ባጭሩ እናያለን፡፡
ሀ. ፕሬዝዳንቱ/ፕሬዝዳንቷ፡-
የሪፓፕሊኩ ርዕሰብሄር፤ የሁለቱንም የፌደራሉን የሕግ አውጭዎች የጋራ ስብሰባ ይከፍታሉ፤
በአመቱ መጀመሪያ የጋራ ስብሰባ የመንግስቱን የአመት ትኩረት እቅዶች የሚገልጽ ንግግር ያደርጋሉ፤
መንግስቱ ስራውን በሕገመንግስቱ መሰረት ማከናወን ካልቻለ በጠቅላይ ሚንስትሩ ጥያቄ ፓርላማውን በመበተን በስድስት(6) ወራት ውስጥ ጠቅላላ ምርጫ እንዲካሄድ ያደርጋል፤
ፓርላማው ያጸደቀውን አዋጅ በፊርማው ያውጃል፤
በሀገሪቱ ፍርድቤቶች የሚወሰንን የሞት ቅጣት በፊርማ የማጽደቅ፣ወደ ዕድሜ ልክ የመቀየር፣ ታራሚዎችን የይቅርታ ቦርድ በሚያቀርበው ግምገማ ላይ በመመስረት ምህረት የማድረግ፤
በጠቅላይ ሚንስትሩ አቅራቢነት የአንባሳደሮችን ሹመት፣ የከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችን የማዕረግ ዕድገትና የጀብዱ ሽልማት ይሰጣሉ፤
የውጭ ሀገራት አንባሳደሮችንና ልዩ መልዕክተኞችን ሲመጡ የሹመት ደብዳቤያቸውን ሲሄዱም የስንብት ደብዳቤያቸውን ይቀበላሉ፤
የሰልጣን ዘመናቸው ስድስት አመት ሲሆን በስልጣን ከሁለት ጊዜ በላይ መመረጥ አይችሉም፡፡
የተመረጡት ከፓርላማ አባላት ውስጥ ከሆነ ሲመረጡ የፓርላማ መቀመጫቸውን ይለቃሉ፡፡ ሹመታቸውም የሚጸድቀው በፓርላማው አቅራቢነት በሁለቱም ምክርቤቶች ፊት ቀርበው ቃለምሃላ ሲፈጽሙ ይሆናል፡፡
ለ. ጠቅላይ ሚንስትር፡-
ርዕሰመንግስት ናቸው፤
የሚንስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢና የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ናቸው፤
የሚመረጡት ከፍተኛውን የወንበር ብልጫ ካገኘው ፓርቲ ሆኖ ሹመታቸው በቀጥታ በፓርላማ የሚጸድቅላቸው ይሆናል፤
የመንግስታቸውን ወይም የአስፈጻሚ አባላት ሚንስትሮችን አቅርበው በፓርላማው ፊት ያስጸድቃሉ፤
የሚንስትር ዴታዎችን፣ ኮሚሽነሮችን፣ በሚንስትር ማዕረግ የሚሾሙ ሀላፊዎችን በቀጥታ ይሾማሉ፤
የፌደራል ፍርድቤቶችን ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት፤ የጀነራል ኦዲተር ዋና ኦዲተር ሃላፊዎችን በመምረጥ ያስሾማሉ፤ የፌደራል ዳኞችን በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አቅራቢነት ለፓርላማው በማቅረብ ያስሾማሉ፤
የስልጣን ዘመናቸው የአምስት አመታት ወይም አንድ የፓርላማ ዘመን ሲሆን ተደጋግመው መመረጥ የሚከለክላቸው የሕገመንግስት ድንጋጌ የለም፡፡
ቸር ይግጠመን!!
ሲሳይ ሰማኝ
Comments
Be the first to add a comment