የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
የትራፊክ ክስ ቻርጅን አልቀበልም ማለት በእስራት እንደሚያስቀጣ ያውቃሉ?
እንሆ ለውድ ተከታታዬቻችን ለጥንቃቄ ይረዳዎ ዘንድ
እንደሚከተለው አቅርባለሁ
የመንገድ ትራፊክ ደንብን መተላለፍ በአብዛኛው በገንዘብ ቅጣት ብቻ የሚያስቀጣ ጥፋት ነው። በአብዛኛው ያልኩት ጥፋቱ በሰው አካል ወይም ህይወት ላይ ጉዳት ካስከተለ የእስራት ቅጣትን ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ ነው።
ሆኖም ግን “የደንብ መተላለፍ ጥፋት ፈፅመሀል” ተብሎ በትራፊክ ፖሊስ የክስ ቻርጅ የተቆረጠለት አሽከርካሪ የክስ ቻርጁን ለመቀበል እምቢተኛ ከሆን እስከ አምስት ዓመት ሊደርስ በሚችል እስራት ሊቀጣ ይችላል። ይህ ድሜዳሜ ንድፈ ሀሳብን (theory) መሰረት ያደረገ ሳይሆን በተግባር ሆኖ የታየና በሁሉም የሀገራችን ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅነት ባለው የሰበር ችሎት ውሳኔ ጭምር ድጋፍ ያለው ነው።
‘’በተግባር ሆኖ የታየ ነው’ ስልም በማስረጃነት የምገልፀው የከፈለ ሰፈነን ጉዳይ ነው።
ከፈለ ሰፈነ በሰሜን ጎንደር ዞን ውስጥ የሠ/ቁጥር 3-28371 አ/አ ተሽከርካሪን የመንጃ ፍቃድ ሳይዝ ሲያሽከረክር ያገኘችው የትራፊክ ፖሊስ የደንብ መተላለፍ ክስ አዘጋጅታ ስትሰጠው ለመቀበል ፍቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት “የመንግስት ስራን ማደናቀፍና የመተባበር ግዴታን መጣስ” የሚል ርዕስ ያለው የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 438 ተጠቅሶበት በቅድሚያ በወረዳ ፍርድ ቤት ክስ ተመሰረቶበት በተጠቀሰው አንቀፅ ስር ጥፋተኛ ነው ተብሎ በአንድ አመት ከስድስት ወር እስራት እንዲቀጣ የተወስነበት: በዃላም ለሰሜን ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ የጥፋተኛነት ውሳኔው ፀንቶበት ቅጣቱን ግን ወደ አንድ አመት እስራት የተቀነሰለት ግለሰብ ነው።
የከፈለ ጉዳዩ ለፌደራል ሰበር ችሎትም ቀርቦ በሠ/መ/ቁጥር #73953 የታየ ሲሆን የፌደራል ሰበር ችሎትም የከፈለን ድርጊት (የትራፊክ ክስ ቻርጅ አልቀበልም ማለቱ) በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 438 ስር የሚወድቅ መሆን አለመሆኑን በስፋት ከመረመረ በዃላ ድርጊቱ በተጠቀሰው አንቀፅ ስር “የሚሸፈን ነው” በማለት በጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠውን የጥፋተኝነት ውሳኔና የ1 ዓመት የእስራት ቅጣት በማፅናት ወስኗል።
የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 438 ድንጋጌ “የመንግስትን ሥራ ማደናቀፍና የመተባበር ግዴታን መጣስ” የሚል ርዕስ ያለው ሆኖ ሙሉ ድንጋጌውም፦
"ማንም ሰው ከመንግስት ሥራ ጋር በተያያዘ ሁኔታ በሕግ በተፈቀደው ወይም ከፍርድ ቤት በተሰጥ ትዕዛዝ መሰረት በመንግስት ሠራተኛ ሲጠየቅ ቀርቦ ለማስረዳት፤ ተገቢውን መልስ ለመስጠት ሰነዶችን ለማቅረብ ወይም ለማስመርመር ወይም ልዩ ልዩ ቤቶችን፥ ቦታዎችን፥ ወይም ሰነዶችን ለማስፈተሽ እምቢተኛ ከሆነ፤ በጠቅላላው ለምርመራ ያልተባበረ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ የመንግስት ስራን ያደናቀፈ እንደሆን፥
ከአምስት አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል።"
=================
የሚል ነው።
የሰበር ችሎቱ ከዚህ ድንጋጌ ውስጥ “በሕግ በተፈቀደው. . .“ እና “በማናቸውም ሌላ መንገድ. . .” የሚሉትን ሁለት ሀረጎች ነጥሎ በመውሰድ “የተከሳሹ ድርጊት በዚህ አንቀፅ ስር የሚሸፈን ነው” ሲል አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል።
ይህ አተረጓጎም ከሌሎች የወንጀል ሕግ መርሆች (ለምሳሌ፦ በይመሳሰላል የወንጀል ድርጊት ተፈፀመ ሊባል የማይችል መሆኑ - የወ/ሕ/ቁ 2(3)) ጋር በማነፃፀር "ትክክል አይደለም" የሚል ክርክር ማንሳት የሚቻል ቢሆንም የሰበር ችሎቱ ውሳኔ አስገዳጅነት ያለው በመሆኑ ክርክሩ (ይህ ውሳኔ ቢያንስ በሌላ የሰበር ውሳኔ እስኪሻር ድረስ) በየትኛው የሀገራችን ፍርድ ቤቶች ተቀባይነት የሚያገኝ ነው።
ምንጭ
በይነ መረብ
የወንጀል ህግ
mr zee
Comments
Be the first to add a comment