የዉክልና ህግ
ዉክልና ማለት አንድ ሰዉ (የተፈጥሮም ሆነ በህግ ሰዉነት ያለዉ) አንድን ስራ በተለያየ ምክንያት በራሱ ቀርቦ ማከናወን ካልቻለ ሌላ ሰዉ ተክቶ የሚያሰራበት ስነ-ስርዓት ነዉ፡፡ በዉክልናም የተለያዩ ሰዎችች ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ዘመድ፣ የህግ ባለሙያ፣ ማናጀሮች እና የመሳሰሉትም መወከል የሚችሉ ሰዎች ናቸዉ፡፡
የኢትዮጵያ ፍትሐብሔር ህግም በመጽሀፍ 4 ስር ስለ ዉክልና በአንቀጾች ከፋፍሎና አብራርቶ ያስቀምጣል፡፡ በአንቀጽ 2198 ላይም ለዉክልና ትርጉም ሲሰጥ “ዉክልና ማለት ተወካይ የተባለ አንድ ሰዉ ወካይ ለተባለዉ ሰዉ እንደራሴ ሆኖ አንድ ወይም ብዙ ህጋዊ ስራዎች በወካዩ ስም ለማከናወን ግዴታ የሚገባበት ዉል ማለት ነዉ፡፡” በማለት ያስቀምጣል፡፡ ዉክልናም ከዉል ወይም ከህግ ሊመነጭ ይችላ፡፡ 
ከዉል የሚመነጭ ዉክልና
ከዉል የሚመነጭ ዉክልና ተወካይ ወኪሉን ተክቶ ሊሰራ የሚችለዉን ስራ በስምምነት የዉል ህጉን በተከተለ መልኩ የሚያደርጉት ስምምነት ነዉ፡፡ አንድ ዉልም በህጉ መሰረት የተደረገ ነዉ ሊባል የሚችለዉ በፍትሐብሔር ህጉ አንቀጽ 1678 እንዳስቀመጠዉ፡-
ተዋዋዮቹ ዉል ለመዋዋል ብቁ የሆኑ እና ፈቃዳቸዉን የሰጡ መሆናቸዉ፡፡ ይህም ማለት ተወካዩም ሆነ ወካዩ ፈቃደኛ ሳይሆኑ በማስገደድ ዉክልና እንዲሰጡ ወይም እንዲቀበሉ ማድረግ አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል ዉሉ በህጻናት፣ የአይምሮ እክል ባለባቸዉ ወይም በህግ ክልከላ በተደረገባቸዉ  መካከል የተፈጸመ መሆን አይችልም፡፡  
በዉሉ ሊሰራ የታሰበዉ ህጋዊ፣ሊፈጸም የሚችልና በበቂ ሁኔታ የተገለጸ መሆኑ፡፡ አንድ ዉል ሲፈጸም ዉሉ ምን ሊሰራ እንደታሰበ በግልጽ ማስቀመጥ አለበት፡፡ ይህም ከተደረገ በኋላ በዉሉ ላይ እንዲፈጸም የተቀመጠዉ ጉዳይ በህግ የተከለከለ ወይም ከማህበረሰቡ ህልዉና ጋር ተቃራኒ የሆነ ወይም ሊፈጸም የማይችል (impossible) መሆን የለበትም፡፡ 
ዉሉ በህጉ በተለየ መልኩ እንዲፈጸም የታዘዘ ከሆነ በዛዉ መልኩ መፈጸም አለበት፡፡ ይህም ማለት ዉሉ በጽሁፍ እንዲደረግ ህጉ የሚያስገድድ ከሆነ ይህን የተከተለ መሆን አለበት፡፡
እነዚህም መስፈርቶች ተሟልተዉ ካልተገኙ የዉክልና ዉሉ ሊፈርስ ወይም ሊሰረዝ ይችላል፡፡ ነገር ግን የነዚህ ነገሮች አለመሟላት በቅን ልቦና ዉል የሚገባን ሶስተኛ ወገን በምንም መልኩ ሊጎዳዉ አይገባም፡፡


ከህግ የሚመነጭ ዉክልና
ከህግ የሚመነጭ ዉክልና ማለት በህጉ ላይ በግልጽ ዉክልና የሚሰጣቸዉ ተወካዮች የሚያገኙት ስልጣን  ማለት ነዉ፡፡በዚህ አይነቱ ዉክልናም ተወካዩ ዉክልና ለመስጠት ፈቃዱ አያስፈልግም፡፡ይህም የሆነበት ምክንያት ተወካዩ ዉክልና ለመስጠት ብቁ ባለመሆኑ ነዉ፡፡ለምሳሌ አንድ ህጻን ልጅ ወይም የአይምሮ እክል ያለበት ሰዉ ማንኛዉንም አይነት በህግ ዉጤት ያለዉ ስራ ሊሰራ አይችልም በዚህም ይህ ችግር ያለበት ሰዉ ፈቃዱን መስጠት ሳያስፈልገዉ ተወካይ በህጉ ሊመደብለት ይችላል፡፡
የዉክልና አይነት  ጠቅላላ ወይም ልዩ ዉክልና ሊሆን ይችላል፡፡ 
ጠቅላላ ዉክልና ተወካዩ በወካዩ ምትክ በመሆን ማንኛዉንም አይነት የአስተዳደር ስራዎችን መስራት የሚያስችለዉ የዉክልና አይነት ነዉ፡፡ በፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 2204 ላይም የአስተዳደር ስራዎች ምን ሊያካትት እንደሚችል ያስቀመጠ ሲሆን በአጭሩ ሲቀመጥ ከወካዩ ንብረት ላይ የሚገኝን ገቢ እና የሚከፈል እዳን የመሰበሰብ፣ ንብረቱን መጠበቅ እና መንከባከብ እና ለተከፈለ እዳ ደረሰኝ መቁረጥ ናቸዉ፡፡
ልዩ ዉክልና  የሚባለዉ ደግሞ ከአስተዳደር ዉክልና ዉጪ ያለ ተግባር ለመፈጸም ለተወካዩ የሚሰጥ ስልጣን ማለት ነዉ፡፡ በፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 2205 ላይም ልዩ ዉክልና ምን ሊያካትት እንደሚችል ተቀምጧል፡፡ በዚህም አንድ ተወካይ ንብረቶችን መሸጥ፣አሲዞ መበደር፣ዉል መፈራረም፣ መታረቅ ስጦታ ማድረግ፣ እና በአንድ ጉዳይ ፍርድ ቤት ቀርቦ መከራከር ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ አይነት ስልጣን በግልጽ በወካዩ መሰጠት አለበት፡፡
ፍርድ ቤት ቀርቦ ለመከራከር የሚሰጥ ዉክልና  
የፍትሐብሔር ስነ-ስርዓት ህግ በአንቀጽ 58 ላይ በፍርድ ቤት ላይ ማን ቀርቦ መከራከር እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡ ፍርድ ቤት ወይም ህግ በግልጽ ወካዩ እራሱ በአካል ቀርቦ እንዲከራከር የሚደርግ ሁኔታ ከሌለም በስተቀር አንድ ሰዉ (የተፈጥሮም ይሁን በህግ ሰዉነት ያገኘ) በቤተሰብ፣ በጠበቃ፣ በነገረ ፈጅ ወይም ማንኛዉም በተቋሙ የተወከለ ሰዉ አማካኝነት በፍርድ ቤት ሊወከል ይችላል፡፡ በቤተሰብ መወከል ሲባልም በዚሁ አንቀጽ ላይ “የዋናዉ ባለጉዳይ ባለቤት፣ ወንድም፣ እህት ልጅ፣ አባት፣ አያት የሆኑ ሰዎች ለዉክልናዉ ዌም ለነገረ ፈጅነቱ አበል ሳይሰጣቸዉ ለመከራከር” እንደሆኑ ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም ከነዚህ ዉጪ ያሉ የቤተሰብ አባላት መወከል አይችሉም፡፡ 
ስለ ዉክልና መቅረት
ዉክልና ቀሪ ሊሆን ወይም ሊሰረዝ የሚችለዉ፡-
ወካይ ወይም ተወካይ ሲሞት
ወካይ ወይም ተወካይ ችሎታ ሲያጡ ማለትም በህጉ ችሎታ ያጣ ሰዉ ከሆኑ
ተወካይ ስራ ለመስራት ችሎታ ያጣ ከሆነ 
ወካይ ወይም ተወካይ ሌላ ስምምነት ከሌለ በቀር ኪሳራ የደረሰባቸዉ እንደሆነ  
ወካዩ ዉክልናዉን በገዛ ፍቃዱ ያነሳዉ እንደሆነ
ተወካይ ለወካዩ በማሳወቅ ዉክልናዉን የተወዉ እንደሆነ
የዉክልና ስልጣን ስለመመለስ
ወካይ በማንኛዉም ግዜ ለተወካዩ የሰጠዉን የዉክልና ሰነድ እንዲመልስለት ሊጠይቀዉ ይችላል፡፡ ይህንም በምንም አይነት ስምምነት ማስቀረት አይቻልም፡፡ በሌላ በኩልም ተወካዩ የሚገባኝን ጥቅም አላገኘሁም ብሎ የዉክልና ሰነዱን በማንኛዉም መልኩ አልመልስም ማለት አይችልም፡፡ 
የዉክልናዉ ሰነድ የጠፋ መሆኑን እንደራሴዉ ወይም ተወካዩ ያስታወቀ እንደሆነ በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2185 መሰረት በተወካዩ ኪሳራ በፍርድ ቤት እንደራሴነቱ እንዲሰረዝለት ወካዩ አመልክቶ ዉሳኔ ማግኘት ይችላል፡፡ 
በቦሌ/ክ/ከ/የህግ/ስ/ህግ/ማ/ዳ
ዐ/ህግ ውብአለም መስፍን

Comments

Be the first to add a comment