👉"የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሀገር የሥልጣኔ ማሳያ እንዲሆን ሥራዎችን በትብብር ማከናወን ይገባል"
- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

💫የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሀገር የሥልጣኔ ማሳያ እንዲሆን ሥራዎችን በትብብር ማከናወን ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሸቲቭን በዛሬው ዕለት ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ዘርፉ በኢትዮጵያ ከሶስት ሺህ ዓመት በላይ ታሪክ ያለው ነው።

ነገር ግን በሚጠበቅበት ልክ አላደገም።

መንግስት የዘርፉን ስብራት ለመጠገን ጨርሶ የመጀመር እና ፕሮጀክቶችን በጊዜ ገንብቶ የማጠናቀቅ ባህልን ለዘርፉ እያስተዋወቀ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም ቀንና ሌሊት የመስራት ልማድ፣ የፕሮጀክት ክትትል፣ ገንዘብን ለታለመለት ዓላማ ማዋል ተችሏል ብለው፤ ይህም የግሉ ዘርፍ ልማድን እየቀየረ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢኒሼቲቩ የአሰሪዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች የሚመዘኑበት ሥርዓት እንዲሁም በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን የሚፈታ መሆኑን የገለፁት አቶ ተመስገን፤ ትግበራው ለ25 ዓመታት እንደሚቆይ ገልፀዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒሰቴር ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ በአሥር ዓመት እቅዱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዲያድግ፣ ለዘርፉ አገልገሎት ከውጭ የሚገቡ በሀገር ውስጥ እንዲተኩ እንዲሁም በዘርፉ ከፍተኛ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።

ለዚህም ሲባል ኢኒሼቲቩ ሲዘጋጅ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ጋር ምክክር መደረጉን አንስተው፤ ከ50 በላይ ባለሙያዎችም ለኢኒሼቲቩ ግብዓት ሰጥተውበታል ሲሉ ገልጸዋል።

ይህም የሰው ኃይል ልማት ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ኢኒሼቲቩ በዘርፉ ሥራ መስራት አስቸጋሪ እንዳይሆን፣ ዘርፉ ተወዳዳሪና ለሀገር እድገት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የሚያደርግ መሆኑንም ገልፀዋል።

Via ጋዜጣ ፕላስ

@etconp

Comments

Be the first to add a comment