የሽያጭ ውልን የተመለከቱ አንዳንድ ነጥቦች
በሙሉ ቀን ሰኢድ ሀሰን እንደተጻፈው፡
መግቢያ
በዚህ ጽሑፍ የሽያጭ ውል ምንነት፣ የማይንቀሳቀስ ንብረት የገዛ ሰው ስላለው መብትና ገዥው ስለሚኖርበት ግዴታ፣ የሽያጭ ውልን መሰረት አድርገው የሚቀርቡ ክርክሮች ይዘታቸው እና የይርጋ ገደባቸው ምን እንደሚመስል እንዲሁም የማይንቀሳቀስ ንብረት የገዛ ሰው ንብረቱን ሊለቅ የሚችልባቸው የሕግ አግባብ ምን ምን እንደሆኑ ከፍትሐብሔር ሕግ እና ከሰበር ውሳኔዎች አንጻር ዳሰሳ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡
1. የሽያጭ ውል ማለት ምን ማለት ነው
በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2266 ላይ እንደተገለጠው የሽያጭ ውል ማለት በሻጭና በገዥ መካከል አንድን ነገር አስመልክቶ አንደኛው ወገን የተወሰነ ገንዘብ (price) ለመክፈል ሌላኛው ወገን ደግሞ ዕቃውን ከነ ባለሀብትነቱ ለማስረከብ የሚገቡት ውል ነው፡፡
በዚህ የሽያጭ ውል ትርጉም ውስጥ ጎልተው የሚወጡ ነጥቦች
• የሽያጭ ውል ልዩ ውል መሆኑና በሁለት ወገኖች መካከል የሚካሄድ መሆኑ፤
• ገዥ የሚባለው ወገን ገንዘቡን ለመክፈልና ሻጭ የሚባለው ወገን ደግሞ የሽያጭ ውሉ አላማ የሆነውን ነገር (ዕቃ) ባለሀብትነት ለገዥው ለማስተላለፍ ግዴታ የሚገቡበት መሆኑ ናቸው፤
• ገዥው ከሻጩ የሚረከበው ዕቃ ዋጋ በገንዘብ ተተምኖ በሽያጭ ውሉ ላይ መገለጽ ይኖርበታል፡፡
በሌላ አነጋገር የሽያጭ ውል በሁለቱም ወገኖች ዘንድ የግዴታ መቋቋምና መፈጸም የሚያስከትል ሆኖ ይህም ባህሪው በአንደኛው ወገን ላይ ብቻ ግዴታ ከሚጥሉ እንደ የስጦታ ውል ካሉ ልዩ ውሎች የሚለየው ነው፡፡ የሽያጭ ውል በባህሪው የችሮታ (gratuitous) ባህሪ የለውም፡፡
ከሽያጭ ውል አይነተኛ ባህሪያት አንዱ ባለሀብትነትን ለገዥ ማስተላለፉ ነው፡፡ ይህም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2281-86 ተመላክቶ ይገኛል፡፡ ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያትም የሽያጭ ውል አላማ ገዥን ባለቤት ማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ሻጩ ዕቃውን ለገዥ ከማስረከቡ በተጨማሪ ባለቤትነትን ማስተላለፍ አለበት፡፡ ባለቤትነት በዋናነት በሕግ ወይም በውል ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ባለቤትነት በሕግ ከሚተላለፍባቸው መንገዶች አንዱ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1161 ላይ የተጠቀሰው የቅን ልቦና ባለይዞታነት (good faith acquisition) መሰረት ነው፡፡ ባለቤትነት በውል ሲተላለፍ የተላለፈለት ወገን ገዥ ከአስተላላፊው ሻጭ ያነሰ መብት ሊኖረው አይችልም፡፡ ይህ ሀሳብ በላቲን /nemo dat qua non habet/ የሚባለው ሲሆን ትርጉሙ ማንም የሌለውን መብት ( ባለቤትነት) ሊያስተላልፍ አይችልም ነው፡፡ በመሆኑም ሻጭ መብቱን ከማስተላለፉ በፊት በርግጥ የባለቤትነት መብት ያለው መሆን መቻል ይኖርበታል፡፡
2. የማይንቀሳቀስ እና ልዩ ተንቀሳቃሽ ንብረት ገዥ ስላለው መብቶች እና የሻጭ ግዴታዎች
ሻጭ የማይንቀሳቀስ ንብረት ከሶስተኛ ወገን ይዞታና ቁጥጥር ነጻ በማድረግ የማስረከብ ግዴታ አለበት፡፡ ይህ ግዴታ ገዥ ለሻጭ ከሚሰጠው የመነቀል ዋስትና ግዴታ የተለየ ነው፡፡ ሻጭ ንብረቱ ላይ የሰፈሩትንና በንብረቱ መዝገብ የተመዘገበ መብት የሌላቸውን ሰዎች የማይንቀሳቀስ ንብረት እንዲለቅቁ በማድረግ ለሻጭ የማስረከብ ግዴታ የማይንቀሳቀስ ንብረት ውል በመፈጸም ሂደት ገዥ ለሻጭ ሊያከናውነው የሚገባ የመጀመሪያ ግዴታ ነው፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2882 እና ተከታይ ድንጋጌዎች መሰረት ሻጭ ለገዥ የሸጠለት የማይንቀሳቀስ ንብረት የማይንቀሳቀስ ስለመሆኑ የሚሰጠው ዋስትና ገዥ የገዛውንና የተረከበውን የማይንቀሳቀስ ንብረት ከሌሎች ሰዎች ቁጥጥር ነጻ ሆኖ ከተረከበ በኋላ ንብረቱ የእኔ ነው ባይ ቢመጣ ሻጭ በዋቢነት ሊቆምለት የሚገባ መሆኑን የሚያመላክቱ ድንጋጌዎች ናቸው፡፡
ገዥ የቤቱ ባለሀብትነት መብት በሽያጭ ውል ከሻጭ የተላለፈለት መሆኑን የሚያሳይ የሽያጭ ውል ሰነድና በሽያጭ ውሉ መሰረት በማይንቀሳቀሰው ንብረት ባለኃብትነት የተዛወረለት መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ በማያያዝ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1206 መሰረት ክስ ለማቅረብ የሚያስችል መብትና ጥቅም አለው ወይስ የለውም? የሚለው ጉዳይ በፍርድ ቤቶች ዘንድ ክርክር ሲካሄድ ይስተዋላል፡፡ በአንድ አንድ ችሎቶች ገዥ የቤቱን ሻጭ ከመክሰስ በስተቀር በቀጥታ በተሸጠው ቦታ ላይ ቤት ሰርተው የሚኖሩ ሰዎች ቤቱን እንዲለቅቁ ክስ ማቅረብ አይችልም በማለት ውሳኔ ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 100395 በቅጽ 21 ላይ ትርጓሜ የሰጠ ሲሆን ትርጓሜውም “ገዥ ሻጭ በሽያጭ ውሉ መሰረት የተሸጠውን ቤት የያዙትን አስለቅቀው ያስረክቡኝ በሚል ክስ ሲያቀርቡ በማይንቀሳቀሰው ንብረት ላይ በማናቸውም ሁኔታ የሚገኙ ሰዎችን በተከሳሽነት አጣምረው መክሰስ እንዳለባቸው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 36(4) አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ ይደነግጋል፡፡ ይህም ሻጭን በሚከሱበት ጉዳይ የተሸጠውን ቤት የያዙትን የግድ በተከሳሽነት እንዲሳተፉ ማድረግ የሚገባ ነው፡፡ በፍርድ ቤቶች ገዥ ሻጭን ከመክሰስ በስተቀር በተሸጠው ቦታ ላይ ቤት ሰርተው የሚኖሩ ሰዎች ቤቱን እንዲለቅቁ ክስ ማቅረብ አይችልም በማለት የሚሰጡት ውሳኔ ሻጭ በሽያጭ በተላለፈው ንብረት ላይ ያለውን መብትና ጥቅም ለማስከበር ገዥው ከውል የመነጨ መብት ያለው መሆኑን ያላገናዘበና የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1195፣ 1206 እና የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 33(2)ን ድንጋጌዎች ያላገናዘበ በመሆኑ ስህተት ያለበት ነው” በማለት ወስኗል፡፡
የመኪና ሽያጭ፡ የመኪና ሽያጭን በተመለከተ ሻጭ ከመኪናው ጋር በተገናኘ ከመኪናው ጋር የተያያዙ አስፈላጊ ሰነዶችን ለገዥ አሟልቶ ያስረከበ መሆኑ ከተረጋገጠ ገዥ ስመ ኃብቱ በስሜ አልተዘዋወረም በሚል ምክንያት ብቻ ውሉ እንዲፈርስ የሚያቀርበው አቤቱታ ተቀባይነት የሌለው ሲሆን ስመ ሀብቱን ለማዞር አስፈለጊ ሁኔታዎችን አሟልቶ ስም እንዲዘዋወርለት ለሚመለከተው የአስተዳደር አካል ጥያቄ አቅርቦ መብቱ ሊረጋገጥለት ያልቻለ ሰው መብቱን የሚያስጠብቀው በሚመለከተው አካል ላይ በፍርድ ቤት ክስ በመመስረት እንጂ ውሉ እንዲፍርስለት በመጠየቅ አይደለም በማለት የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 56569 በቅጽ 12 ላይ የህግ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡
3. የሽያጭ ውል አለመፈጸም ስለሚያስከትለው ውጤት
ተዋወይ ወገኖች ያቋቋሙት ውል አለመፈጸሙ ልዩ ልዩ ውጤቶችን ያስከትላል፡፡ አንድ ግዴታ እንደውሉ አልተፈጸመም የሚባለው
• ውሉ ሙሉ በሙሉ ካልተፈጸመ
• ውሉ በከፊል ተፈጽሞ በከፊል ደግሞ ካልተፈጸመ ነው፡፡
እንደ ውሉ አልተፈጸመም የሚል ወገን ሁለት መፍትሔዎች ይኖሩታል፡፡
1ኛ) ውሉን በግዴታ ማስፈጸም
2ኛ) ውሉን ማፍረስና ካሳ መጠየቅ (1784-1789) ይህም በነጠላ ማለትም በአንደኛው ወገን ከሳሽነት ወይም በፍርድ ቤት አጽዳቂነት ሊፈጸም ይችላል፡፡
ጉድለት ያለበት ንብረት ወይም ደግሞ ሙሉ የባለቤትነት መብት ለመገልገል የማያስችል ጉድለት ያለበት ንብረት የተረከበ ገዥ ያለው የማስተካከያ መብት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2336 እና ቀጥሎ ባሉት ድንጋጌዎች የተጓደሉትን ነገር አሟልቶ ይፈጸም ዘንድ ወዲያውኑ መጠየቅ ሲሆን ከዚህ ጋር ጎን ለጎንም በፍ/ብ/ህ/ቁ 2360 እንደተመለከተው ከላይ ከተመለከቱት የህግ መፍትሔዎች በሻጭ ግዴታ መጓደል ምክንያት የደረሰበትን ጉዳት በገንዘብ አስልቶ መጠየቅ እንደሚገባው ተመልክቷል፡፡
ገዥ የሽያጭ ውል በግድ እንዲፈጸምለት ለመጠየቅ የሚችለው ልዩ የሆነ ጥቅም የሚያስገኝለት ሆኖ ሲገኝ ሲሆን ገዥው ውሉ ላይ ልዩ ጥቅም አለው የሚባለው እና የሽያጭ ውሉን ፍርድ ቤቶች ሻጭ በፍርድ ሀይል እንዲፈጽም ለመወሰን የሚችሉት የሽያጭ ስምምነት የተደረገበ

Comments

Be the first to add a comment