ክቡራን ሰላማችሁ ይብዛ!!
የዓለማቀፉ አካልጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ስለተደራሽነቱ የደነገገውንና ሀገራችን በአዋጅ ቁጥር 676/2002 በማጽደቅ የሕጎቿን አካል በማድረግ ለተፈጻሚነቱ ግዴታ የገባችለትን እንደሚከተለው ይድረስልኝ፡!
ተደራሽነት የሚመለከተው አንቀጽ 9 ነው፡፡
አካል ጉዳተኞች ኑሯቸውን በነፃነት እንዲመሩና በየትኛውም የሕይወት መስክ ያልተገደበ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል ተዋዋይ መንግሥታት እነዚሁ ወገኖች ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር ባልተናነሰ ሁኔታ ቁሳዊ አካባቢን የመድረስም ሆነ በመጓጓዣ ዘዴዎች፣ የመረጃና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችንና ስርዓቶችን ጨምሮ በመረጃና መገናኛ አውታሮች እንዲሁም በከተማም ይሁን በገጠር ለሕዝብ ክፍት በተደረጉ ተቋማትና አገልግሎቶች የመጠቀም ዕድል የተመቻቸላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ተገቢነት ያላቸውን እርምጃዎች ይወስዳሉ፡፡
በተደራሽነት ላይ የተጋረጡትን መሰናክሎችና ገደቦች መለየትና ማስወገድን የሚያጠቃልሉት እነዚህ እርምጃዎች ከሁሉ በፊት ቀጥሎ በተመለከቱት ላይ ተፈፃሚዎች ይሆናሉ፡፡
ሀ) ሕንፃዎች፣ መንገዶች፣ የመጓጓዣ ዘዴዎችና እንደ ትምህርት ቤቶች፣ የመኖሪያ ሥፍራዎች፣ የሕክምና አገልግሎት መስጫ ድርጅቶችና የስራ ማከናወኛ ቦታዎች ያሉ የቤት ውስጥና የቤት ውጭ መገልገያ ተቋማት!
ለ) የኤሌክትሮኒክስና የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎቶችን ጨምሮ የመረጃ፣ የመገናኛና ሌሎች አገልግሎቶች፡፡
2. ተዋዋይ መንግስታት በተጨማሪ ከዚህ በታች የተመለከቱትን በስራ ላይ ለማዋል ተገቢ እርምጃዎችን ይወስዳሉ፡፡
ሀ) ለሕዝብ ክፍት የተደረጉ ወይም የተመቻቹ ተቋማትንና አገልግሎቶችን ለመድረስ የሚያስችሉ ዝቅተኛ መስፈርቶችንና መመሪያዎችን ማዘጋጀት፣ በይፋ ማውጣትና ተግባራዊነታቸውን መቆጣጠር!
ለ) ለሕዝብ ክፍት የሆኑ አገልግሎቶችን በማመቻቸትና በማቅረብ ስራ ላይ የተሰማሩ የግል ድርጅቶች እነዚሁ አገልግሎቶች ለአካል ጉዳተኞች ጭምር ተደራሽነት እንዲኖራቸው አስፈላጊ የሆኑትን ጉዳዮች ሁሉ ግምት ውስጥ ማስገባታቸውን ማረጋገጥ!
ሐ) አካል ጉዳተኞችን በሚገጥሟቸው የተደራሽነት ችግሮች ዙሪያ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ወገኖች ስልጠና መስጠት!
መ) ለሕዝብ ክፍት በሆኑ ሕንፃዎችና ሌሎች መገልገያ ተቋማት ውስጥ በግልጽ የሚታዩ ምልክቶችን፣ ብሬሎችንና በቀላሉ አንብቦ ለመረዳት የሚያስችሉ ቅጾችን ማስቀመጥ ወይም ማቅረብ!
ሠ) የቀጥታ ድጋፍ ዓይነቶችንና መሪዎችን፣ አንባቢያንንም ሆነ በምልክት ቋንቋ አጠቃቀም የሰለጠኑ አስተርጓሚዎችን ጨምሮ ለሕዝብ ክፍት የሆኑ ሕንፃዎችንና ሌሎች መገልገያ ተቋማትን ተደራሽነት የሚያመቻቹ አማካዮችን ዝግጁ ማድረግ!
ረ) አካል ጉዳተኞች መረጃ የማግኘት ዕድል የተጠበቀላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሌሎች ተገቢነት ያላቸውን የእርዳታና የድጋፍ ዓይነቶችን ማስፋፋት!
ሰ) አካል ጉዳተኞች የመረጃን መረብን ጨምሮ በአዳዲስ የመረጃና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችና ሥርዓቶች የሚጠቀሙበትን ዕድል ከፍ ማድረግና!
ሸ) ለወደፊቱ በዝቅተኛ ዋጋ ሊቀርቡ የሚችሉበት ዕድል እስኪፈጠር ድረስ ምቹና ተደራሽነት ያላቸውን የመረጃና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችና ሥርዓቶች ዝግጅት፣ ልማት፣ አመራረትና ሥርጭት ከመነሻው ጀምሮ ማስተዋወቅ
የሚል ዝርዝር ካስቀመጠው በመነሳት ይመስላል ኢትዮጵያም የህንጻ አዋጅ 624/2001በአንቀጽ 36 ማንኛውም ህንጻ ለአካል ጉዳተኞች በተሽከርካሪ ወንበር መንቀሳቀስ በሚያመች መለኩ እንዲገነባ፣ መጸዳጃቤቶችም ለአጠቃቀም በሚያመች መልኩ መሰራት እንዳለባቸው፤
ደንግጋ ትገኛለች፡፡
ምቹ የሆነች ኢትዮጵያን ለኛ!!!
ህዳር 18 ቀን 2014 ዓ.ም
ሲሳይ ሰማኝ

Comments

Be the first to add a comment