የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት፡ሌላኛው የኢትዮጵያ አዲስ የስኬት ምዕራፍ

ባለፉት ዓመታት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥና ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት ረገድ ሀገሪቱን ከፍ ያደረጉ አበይት ተግባራት ተከናውነዋል።

ስኬት ከተመዘገበባቸው ተቋማት አንዱ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው።ተቋሙ በየዘርፉ ዐቅሙን እያሳደገ ነው።ለዚህም የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ አሥረጂ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም ባስጀመሩበት ወቅት በሰማይ ለሚበርሩ መርከቦቻችን እንደ ትልቅ ወደብ ሆኖ ያገለግላል፤ይህም ለኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ሥርዓት የዘመናት ስብራት ምላሽ የሚሰጥ ነው ማለታቸው ይታወሳል።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የአፍሪካን አቪዬሽን እድገት ማሳያ እና ትልቅ አርአያ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ከዓለም ቀዳሚ የአቪዬሽን ተርታ የሚያሰልፍ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድገዋል።

በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአቪዬሽን መሠረተ-ልማት ፕሮጀክት በመሆኑም ኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ያላትን አቅም በይበልጥ ከፍ ባለ ኩራት ያስጠራል።

አውሮፕላን ማረፊያው ሀገሪቱን የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና (AfCFTA) ተግባራዊነት ለማቀላጠፍና የአኅጉሪቱን የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

ከአውሮፕላን ማረፊያው ጋር ተያይዞ የሚመሰረተው የኤርፖርት ከተማ በንግድ፣በኢንዱስትሪና በቱሪዝም ዘርፎች ለአካባቢው ዕድገት ትልቅ አስተዋጽዖ የሚኖረው ሲሆን ተጨማሪ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ይፈጥራል።

የፕሮጀክቱ ግዙፍነት እና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን (FDI) ወደ ኢትዮጵያ ከመሳብ በተጨማሪም በግንባታው ወቅት እና ከተጠናቀቀ በኋላ በሚሰጡ አገልግሎቶች በሺዎች ለሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ የሥራ ዕድል ይፈጥራል።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የኢትዮጵያን ታላቅነት በይበልጥ የሚያጠናክር፣የዜጎችን ተጠቃሚነት በየዘርፉ የሚያሳድግ እና ሀገሪቱን ከዓለም ቀዳሚ የአቪዬሽን ተርታ የሚያሰልፍ ሜጋ ፕሮጀክት ነው።

ፕሮጀክቱ በዕውቀት ሽግግር፣በሥራ ዕድል ፈጠራ፣አካባቢውን ብሎም ሀገርን በማልማት ኢትዮጵያን በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ አሁን ካላት አቅም በይበልጥ የሚያስጠራ ነው።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተተገበረው ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመፈጸም አቅም ማረጋገጫ እንደሚሆንም ይጠበቃል።

ሀገሪቱ ታላላቅና ውስብስብ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በጠንካራ አመራር ሰጪነት በመምራት በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት አጠናቆ ለምርቃት በማብቃት ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመሰከላት አዲስ ብሔራዊ የሥራ ባህል ፈጥራለች።

እንደ ምሳሌም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ፣የዓድዋ ድል መታሰቢያን በአጭር ጊዜ መገንባት፣የሳይንስ ሙዚየም፣የኮሪደር ልማቶች እና ዘመናዊ የቱሪስት መናፈሻዎች በጥራት ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው ኢትዮጵያ አሁን ላይ ግዙፍ የኢኮኖሚና የመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶችን የማቀድ፣የመምራትና በተያዘላቸው ጊዜ የማጠናቀቅ አቅምን በተጨባጭ የሚያሳይ ነው።

የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያም ይህንኑ የጽናትና የስኬት ጉዞ በላቀ ደረጃ የሚደግም ይሆናል።

Via ኢዜአ

@etconp

Comments

Be the first to add a comment