የመጥፋት ውሳኔ የሚሰጥባቸው ሁኔታዎች እና የሚያስከትላቸው ውጤቶች

መግቢያ
አንድ ሰው ከሚኖርበት ወይም ከሚሰራበት አካባቢ ርቆ፣ የት እንደደረሰ ሳይታወቅ እና በሕይወት የመኖሩ ነገር አጠራጣሪ ሆኖ ሲቀር፤ ጉዳዩ ከግለሰቡ ባለፈ በቤተሰቡ፣ በንብረቱ እና በሕጋዊ ግንኙነቶቹ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ይፈጥራል። ይህንን ቀውስ ለመፍታት እና መብትና ግዴታዎቹን ሕጋዊ መስመር ለማስያዝ የኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ የመጥፋት ውሳኔ ሥርዓትን ደንግጓል። ይህ ጽሑፍ የመጥፋት ውሳኔን ምንነት፣ የሚሰጥባቸው ሁኔታዎችንና ውሳኔው ስለሚያስከትላቸው ውጤቶች እንዲሁም የመጥፋት ውሳኔ ቀሪ ስለሚሆንባቸው ሁኔታዎች በአጨሩ ይዳስሳል።

የመጥፋት ውሳኔ ምንነት
ታዋቂው ብላክ የሕግ መዝገበ ቃላት በ8ኛ እትሙ መጥፋትን “the state of being away from one’s usual place of residence” (Black’s Law Dictionary, 8th edition) ሲል ይተረጉመዋል። ይህም ወደ አማርኛ ሲተረጎም መጥፋት ማለት ከመደበኛ መኖሪያ ቦታ አለመገኘት የሚል ይሆናል።
በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ ቀጥተኛ የሆነ ትርጉም ባይሰጠውም አንድ ሰው በመደበኛነት ከሚኖርበት ቦታ የተሰወረ እና ከ2 ዓመት ወዲህ ስለመኖሩ ምንም አይነት ፍንጭ ያልሰጠ በመሆኑ ምክንያት የመጥፋት መግለጫ ጥያቄ ለፍርድ ቤት ሲቀርብ እና ጠፋ የተባለው ሰው በሕይወት ስለመኖሩ አጠራጣሪ ሲሆን እና ይህ ሁኔታም ሞተ የሚያስብል ግምት የሚያስወስድ በሆነ ጊዜ ፍርድ ቤት የሚሰጠው ውሳኔ የመጥፋት ውሳኔ እንደሆነ ከፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 154 እና 157 ይዘት መረዳት ይቻላል።

የመጥፋት ውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች
አንድ ሰው ስለመጥፋቱ ፍርድ ቤት ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት በፍትሐብሔር ሕጉ ላይ የተቀመጡ ጥብቅ መስፈርቶች መሟላት አለባቸው። ከእነዚህ መስፈርቶች ውስጥ አስገዳጁ ሁኔታ የማስታወቂያ ሥርዓት ሲሆን የማጣራት ሥራ እንደአስፈላጊነቱ ጥቅም ላይ ይውላል።
 የማስታወቂያ ሥርዓት
የመጥፋት ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሎ ጠፋ የተባለው ሰው በመደበኛነት ይኖርበት በነበረው ቦታ እና ፍርድ ቤት አስፈላጊ ነው ብሎ በሚገምተው ቦታ የተሻለ ነው በሚለው ዘዴ (ጋዜጣ፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን…ወዘተ) ማስታወቂያ በማውጣት ስለግለሰቡ መረጃ ይሰበስባል (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 155)። ይህም ሰውየው በሕይወት ካለ እንዲቀርብ ወይም መረጃ ያለው ሰው እንዲያሳውቅ ያስችላል።
 የማጣራት ሥራ
ከማስታወቂያው በተጨማሪ ፍርድ ቤቱ አስፈላጊ ነው ብሎ ባሰበው ማንኛውም ቦታ ሁሉ ይልቁንም የጠፋው ሰው በመጨረሻ ዋና መኖሪያ አድርጎ ይኖርበት በነበረው ቦታ እና በመጨረሻ ጊዜ መኖሩ በታየበት ቦታ ስለጠፋው ሰው ማጣራት /ምርመራ/ እንዲደረግ ትእዛዝ መስጠት ይችላል (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 156)።
 የመጥፋት ውሳኔ የተፈጻሚነት ጊዜ
ከላይ የተጠቀሱት ሂደቶችን ተከትሎ የጠፋው ሰው ሞተ የሚያስብል ግምት የሚያስወስድ ሆኖ ሲያገኘው ፍርድ ቤቱ የመጥፋት ውሳኔን ይሰጣል። ይህ በሚሆንበት ጊዜም ፍርድ ቤቱ እንደአካባቢው ጠባይ የጠፋው ሰው ንብረቱን የሚያስተዳድርለት ሰው መወከል አለመወከሉን እንዲሁም ስለግለሰቡ ወሬ ላለመገኘቱ ከልካይ የሆኑ ነገሮችን ፍርድ ቤቱ መመርመር እንዳለበት ሕጉ ይደነግጋል (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 157)።
ይሁንና ፍርድ ቤቱ ሲያምንበት የሚሰጠውን ውሳኔ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 158 መሠረት ለ1 ዓመት ያህል ሊያራዝም የሚችል ሲሆን የሠጠው ውሳኔም ከ1 ዓመት በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን ትእዛዝ መስጠት ይችላል።
 የመጥፋት ውሳኔ እንዲሰጥ አቤቱታ የማቅረብ መብት ያላቸው ወገኖች
በፍትሐብሔር ሕጉ የተለያዩ ድንጋጌዎች ሥር እንደተመለከተው ማንኛውም ያገባኛል የሚል አካል የመጥፋት ውሳኔ እንዲሰጥለት ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ ይችላል (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 154(1) ‘…ማንኛውም ባለጉዳይ…’)። ይህ ሲባል ግን ሁሉም ማለት ሳይሆን የሚመለከተው ባለጉዳይ ማለት እንደሆነ ከሌሎች ድንጋጌዎች ንባብ መገንዘብ ይቻላል። ይኸውም ጠፋ የተባለው ሰው ሚስት/ባል (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 163/1/፣ ጠፋ የተባለው ሰው የኑዛዜ/ያለኑዛዜ ወራሾች (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 164 እና 167)፣ ከጠፋው ሰው በውል ወይም በሌላ መንገድ ግዴታ ያለባቸው ሰዎች (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 166) እና ዐቃቤ ሕግ (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 156) የመጥፋት ውሳኔ እንዲሰጥ አቤቱታ የማቅረብ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል።
 ጉዳዩን የማየት ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት
መጥፋትን በተመለከተ የማየት ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት ማን ነው? የሚለውን በተመለከተ በፌዴራል ደረጃ የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች እንደሆኑ ቻርተር አዋጆች ደንግገዋል (የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 አንቀጽ 41፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 416/1996 አንቀጽ 33)። የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 5(1)(ደ) ይህንን ጉዳይ የመዳኘት ሥልጣን የከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች እንደሆነ ይደነግጋል። ሆኖም ግን በሌሎች ክልሎች የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ከመጥፋት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የማየት ሥልጣን አላቸው።

የመጥፋት ውሳኔ የሚያስከትላቸው ውጤቶች
የመጥፋት ውሳኔ በጠፋው ሰው መኖር ምክንያት የሚገቡ ግዴታዎች ላይ እና በመሞቱ ምክንያት በሚገኙ መብቶች ላይ ውጤቶችን ያስከትላል። እነዚህም፡-
 የጋብቻ መፍረስ /Dissolution of Marriage/
በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 163 እና በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75(ሀ) መሠረት በፍርድ ቤት የመጥፋት ውሳኔ ሲሰጥ በጠፋው ሰው እና በሕይወት ባለው የትዳር አጋር መካከል የነበረው ጋብቻ ይፈርሳል። ይህም የሚሆነው የመጥፋት ውሳኔ የመጨረሻ በሆነበት ቀን ነው።
 የውርስ መከፈት እና የንብረት መተላለፍ
የመጥፋት ውሳኔው እንደሞት ስለሚቆጠር የጠፋው ሰው ውርስ ይከፈታል (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 164፣ 165)። ንብረቱ ለሕጋዊ ወራሾቹ ወይም በኑዛዜ ለተጠቀሱ ሰዎች ይተላለፋል። ሆኖም ግን ባለይዞታ የሆነ ሰው የጠፋውን ሰው ልጆች ለማቋቋም ካልሆነ በስተቀር ንብረቱን በስጦታ የማስተላለፍ መብት አይኖራቸውም (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 169)። የጠፋው ሰው በሕይወት የመመለስ ዕድል ግምት ውስጥ ስለሚገባ ወራሾች ንብረቱን ከመረከባቸው በፊት ንብረቱ እንዳይጠፋ ዋስትና እንዲያርቡ ፍርድ ቤት ሊያስገድድ ይችላል (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 168)።

የመጥፋት ውሳኔ ቀሪ ስለሚሆንባቸው ሁኔታዎች
የመጥፋት ውሳኔ በሚከተሉት ምክንያቶች ቀሪ ይሆናል። እነዚህም፡-
• ጠፋ የተባለው ሰው መመለስ፣
• ጠፍቷል የሚል የፍርድ ማስታወቂያ ከወጣ በኋላ በሕይወት ለመኖሩ ማስረጃ ከተገኘ
ወይም
• የመጨረሻ ወሬዎቹ የተሰሙበት ከተባለው ጊዜ በሌላ ጊዜ የሞተ ስለመሆኑ ማስረጃ
የተገኘ እንደሆነ የሚሉት ናቸው (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 170)።

Comments

Be the first to add a comment