የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
ስለ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝዉዉር አስከፊነት ምን ያህል ያዉቃሉ?
የወቅቱ አንገብጋቢ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ህገወጥ-የሰዎች ዝዉዉር ነዉ፡፡ ይህም በተለያዩ የሶሺያል ሚዲያ እና የዜና አዉታሮች በሰፊዉ እየተነሳ ያለ ጉዳይ ነዉ፡፡ ይህንም ተከትሎ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በመዘርጋት ላይ ይገኛሉ፡፡ በሰዉ የመነገድ እና ሰዉን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣዉ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 ዓ.ም መሰረት በማድረግም ደንብና መመሪዎች ወጥተዋል፡፡ ከዚህ አዋጅ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲ የወጣዉ የወንጀል ህግ አዋጅ ቁጥር 414/2016 ዓ.ም ከአንቀጽ 596 ጀምሮ ስለዚሁ ወንጀልና ፈጽሞ የተገኘ ተጠርጣሪ ሊወሰንበት የሚችለዉን የቅጣት አይነት አስቀምጧል፡፡ አዋጁም ሆነ የወንጀል ህጉ በሰዉ መነገድንም ይሁን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የፈጸመን ሰዉ ጥፋተኛ አድርገዉ ይወስዳሉ፡፡ አንድ ሰዉ ወንጀሉ እንደሚፈጸም እያወቀ ቤት ያከራየ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት የሰጠ ይሁን የተለያዩ ወንጀሉ እንዲፈጸም የሚያገለግሉ ሰነዶችን ያዘጋጀ እንደሆነ በእርግጥም ወንጀሉን እየፈጸመ ካለ ሰዉ ጋር ወንጀለኛ ተበሎ ይፈረጃል፡፡ ቅጣቱም ከ 3 አመት እስከ 15 አመት እንደወንጀሉ አፈጻጸም ሁኔታ እንዲቀጣ ያደርጋል፡፡ይህም ቅጣት ቀላል የማይባልና አንድ ሰዉ ወንጀሉን ፈጽሞ ቢገኝና ቢፈረድበት ሌሎች ለራሱም ይሁን ለሃገሩ የሚጠቅም ስራ የሚሰራበትን ግዜ ያላግባብ የሚወስድና ለሃገርም ዉድቀት የሚዳርግ ነዉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በህገ-ወጥ መንገድ ዝዉዉር በሚደረግበትም ግዜ በህይወት ተርፎ መገኘትም አንዱ አጠያያቂ ነገር ነዉ፡፡ በተለያዩ የሚድያ ዘዴዎች እንደምንሰማዉም በተለያዩ በሽታዎች መሞት፣ የሚጓጓዙበት የትራንስፖርት ዘዴዎች አልመች ሲሉ ሰዎችን በመግደል መቀነስ፣ ወደሌላ ቦታ እንወስዳችኋለን ብሎ በመደለል የሰዉነታቸዉን አካል አዉጥቶ መዉሰድ፣ ለተለያዩ የወሲብ ተግባሮች መጠቀሚ ማድረግ እና በመሳሰሉት ተግባራት ከአካል ጉዳት እስከ መሞት ድረስ ለሚያደርስ ጉዳት የሚዳርግ ነዉ፡፡ በመሆኑም ይህን ወንጀል ከመፈጸምም ሆነ እንዲፈጸም እርዳታ ከማድረግ መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወንጀሉን ተቆጣጥሮ እንዲቀንስ ለማድረግ በወጣዉ ደንብና መመሪያ መሰረት ምክር ቤትና የትብብር ጥምረት በመመስረት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በዚህም የተለያዩ ቡድኖች ተመስርተዉ ስለወንጀሉ መስፋፋት መነሻዉ ጀምሮ ተመለላሾችን መልሶ እስከማደራጀትና ግንዛቤ እስከመፍጠር ፈንዶች ማሰባሰብ ድረስ እንዲሰሩ ወደስራ በመግባት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ዉጤታማ ሆኖ ወንጀሉን መቀነስ ይቻል ዘንድ የሁሉም ህብረተሰብ ተሳትፎ አስፈላጊ በመሆኑ ወንጀሉን የሚፈጽሙት በማጋለጥ የዜግነት ግዴታችሁን እንድትወጡ ይህን መልክት እናስተላልፋለን፡፡
የቦሌ/ክ/ከ/ፍ/ጽ/ቤት
የህ/ስ/ም/መ/ዳ ዐ/ህግ ዉብአለም መስፍን
Comments
Be the first to add a comment