ስለደን ምንነትና አይነቶች የጀመርነውን ወግ ለመቀጠል ተመልሰናል!
በቀደመው መልእክታችን የደን ምንነትና ከባለቤትነት አኳያ የደን አይነቶችን ለመመልከት ሞክረናል። ዛሬ ደግሞ ደን ከሚሰጠው ጥቅምና ሊደረግለት ከሚገባው ጥበቃ አንጻር በደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 1065/2010 አንቀጽ 2 ንኡሳን አንቀጾች 11, 12, 13, 14 እና 15 የተዘረዘሩትን ልዩ ልዩ የደን አይነቶች እንመለከታለን!
“ጥብቅ ደን” ማለት ለተለያዩ የሥርዓተ ምህዳር ግልጋሎት የሚውል ደን ሲሆን በሚመለከተው አካል በሚዘጋጅለት የደን ማኔጅመንት ዕቅድ መሠረት የደኑን ዘላቂ ሥርዓተምህዳራዊ ዕሴቶች በማይጎዳ መልኩ በጥቅም ላይ እንዲውል የተለየ ደን ነው፤
“ፍፁም ጥብቅ ደን” ማለት ደኑን ከአደጋ ለመጠበቅ ካልሆነ በስተቀር ከማንኛውም የሰውና የቤት እንስሳት ጣልቃ ገብነት የተጠበቀ ደን ሲሆን ለብዝሀ ህይወት ጥበቃ፣ ለታሪካዊና ለምርምር የተለየ ደን ነው፤
“ምርት ሰጪ ደን” ማለት በዋናነት ለኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች የለማ ደን ነው፤
“ሰው ሰራሽ ደን” ማለት በሰው አማካኝነት የለማ ደን ነው፤
“የተፈጥሮ ደን” ማለት በአብዛኛው በተፈጥሮ የበቀሉ ዛፎች፣ ቁጥቋጦና ሌሎች የእንጨትነት ባሀሪ ያላቸውና የሌላቸው ተክሎችና ዕፅዋቶች ያሉበት ደን ነው፤
“ጥምር እርሻ ደን” ማለት ሰብልንና ዛፍን ወይም የእንስሳት መኖንና ዛፍን ወይም ሶስቱንም በአንድ መሬት ላይ በተመሳሳይ ጊዜ ወይም በማፈራረቅ በቅንጅት በማልማት የሚከናወን የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ስልት በመጠቀም የሚለማ ወይም የለማ ደን ነው፤
ደን ህይወት ነው!
መስከረም 20 ቀን 2015 ኣ.ም
ፋሲካ አጌና (የሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት አቃቤ-ሕግ)

Comments

Be the first to add a comment