የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
የወንጀል ህግ መርሆች
መግቢያ
ወንጀል ማለት በህግ አስቀጪነቱ የተደነገገውን ድርጊት በማድረግ ወይም ባለማድረግ የህግ ተጠያቂነት እና ቅጣትን የሚያከትል ድርጊት ነው። የወንጀል ህግ ደግሞ ወንጀል ስለሆኑ ድርጊቶች እና አለማድረጎች እንዲሁም ቅጣታቸውን የሚዘረዝር የህግ አይነት ነው። የወንጀል ህግ የራሱ የሆኑ መርሆች ያሉት ሲሆን በሀገራችንም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግስት እና የወንጀል ህጉ አለማቀፋዊ ባህርይ ያላቸውን መርሆች አካተው የወጡ ናቸው። በዚህ ፅሁፍ በህገ መንግስቱ እና በወንጀል ህጉ የተደነገጉ የወንጀል ህግ መርሆች በአጭሩ እንመለከታለን።
• የወንጀል ህግ መርሆዎች
“መርህ” ማለት የአንድ ነገር ማጠንጠኛ መሰረት ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን በቀላሉ የማይለወጥ፣ የማይሸረሸር፣ ሊጣስ የማይገባውና ከተጣሰ ግን ያ በሱ ላይ የተመሰረተው ፍሬ ሀሳብ ህልውናው ሊናጋ ስለሚችል መርሁ ወይም መሪው ሀሳብ በሚገባ ሊጠበቅና ሊያዝ የሚገባው ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ደስታ ተክለ ወልድ በአማርኛ የመዝገበ ቃላት መፅሐፋቸው “መርህን” “የመራ፣ የሚመራ፣ መሪ” በሚል የተረጎሙት። በመሆኑም ህጎች ሲወጡም ሆነ ሲተገበሩ የህግ መርሆችን መሰረት ያደረጉ መሆን ይኖርባቸዋል። በአለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገራችን ተቀባይነት ያላቸው እና በሥራ ላይ እየዋሉ የሚገኙ የወንጀል ህግ መርሆችን እንደሚከተለው እንመለከታለን።
1. የሕጋዊነት መርህ (Principle of Legality)፡- የህጋዊነት መርህ
መሰረታዊ ሀሳብ በህግ ከተደነገገው ውጪ ቅጣት ሊኖር አይችልም የሚል ነው። በመሆኑም ማናቸውም ሰው የተከሰሰበት ድርጊት በተፈፀመበት ጊዜ ድርጊቱን መፈፀሙ ወይም አለመፈፀሙ ወንጀል መሆኑን የሚደነግግ ህግ ከሌለ በወንጀል ተጠያቂ ሊሆንና ሊቀጣ አይገባውም የሚል ነው፡፡ አንድን ሰው ሆነ ብሎም ይሁን በቸልተኝነት አንድ ድርጊት ፈፅመሀል ወይም መፈፀም የሚገባህን አልፈፀምክም ብሎ ለመክሰስና በወንጀል እንዲቀጣ ለማድረግ የወንጀል ፈፃሚው ድርጊት ወይም ተዓቅቦ በወንጀልነት የሚፈርጅና የወንጀል ቅጣት የሚደነግግ አስቀድሞ የታወጀ ህግ መኖር አለበት፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ሕገ-ወጥነቱ በህግ ያልተደነገገን ድርጊት ወይም ግድፈት እንደወንጀል ሊቆጥረው እና ቅጣትን ሊወስን እንደማይችል በወንጀል ህጉ እንቀፅ 2(2) ስር ተደንግጎ ይገኛል። እንዲሁም ፍርድ ቤቱ በህግ ከተደነገገው በቀር ሌሎች ቅጣቶችንና የጥንቃቄ እርምጃዎችን መወሰን አይችልም።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ የተመሳሳይነት (analogy) ጉዳይ ሲሆን በህግ ላይ ከተደነገጉት ወንጀሎች ጋር ይመሳሰላል በማለት ወንጀልነቱ በግልፅ ያልተደነገገን ድርጊት ወይም ግድፈት እንደወንጀል ሊቆጠር እንደማይችል የወንጀል ህጉ አንቀጽ 2(3) ይደነግጋል።
2. የወንጀል ሕግ ወደኋላ ተመልሶ የማይሰራ መሆኑ (Non-Retroactivity of Criminal Law)
በዚህ መርህ መሰረት ህግ ሊተገበር ወይም ሊፈፀም የሚችለው ህጉ ከፀደቀ በኋላ በተፈፀሙ ድርጊቶች ላይ ነው። ይህ ማለት አዲስ ህግ ሲወጣ ህጉ ከመውጣቱ በፊት የተፈፀሙት ድርጊቶች በአዲሱ ህግ ወንጀል መሆናቸው ቢደነገግም ለበፊቱ ድርጊት ተፈፃሚ አይሆንም። አንድ ሕግ የዜጎችን መብትና ግዴታ የሚወስን በመሆኑ ሰዎች ሕጉ እስከሚለወጥ ድረስ ድርጊቶቻቸውን ወይም ግንኙነታቸውን ሕጉ በሚፈቅደው ወሰን ውስጥ ያካሂዳሉ፡፡ አንድን ሁኔታ የሚለውጥ ወይም የሚያሻሻል ሕግ ቢወጣ ሕጉ ተፈፃሚ መሆን ያለበት ቢያንስ ከታወጀበት ቀን ጀምሮ ወደፊት መሆን አለበት፡፡
ይህ መርህ በወንጀል ህግ አንቀፅ 5 እና በህገ መንግስቱ አንቀፅ 22 ስር ተደንግጎ ይገኛል። በዚሁ መሰረት በአዲሱ ወይም በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግ እና በተሻረው የወንጀል ህግ እንደወንጀል የተቆጠረ ድርጊት የተፈፀመው አዲሱ ህግ ከመፅናቱ በፊት ከሆነ፣ ጉዳዩ የሚታየው በተሻረው የወንጀል ህግ መሰረት ነው። ድርጊቱ በአዲሱ ህግ መሰረት ወንጀል ሆኖ በተሻረው ህግ ግን እንደወንጀል ካልተቆጠረና የተፈፀመው አዲሱ ህግ ከመፅናቱ በፊት ከሆነ ሊያስቀጣ አይችልም። እንዲሁም የተሻረው ህግ ይሰራ በነበረበት ጊዜ የተፈፀመ ወንጀል ሲኖር በአዲሱ ህግ ግን እንደወንጀል ያልተቆጠረ ሲሆን ሊያስከስስም ሆነ ሊያስቀጣ አይችልም፤ ክሱም ተጀምሮ እንደሆነ እንደሚቋረጥ በወንጀል ህጉ ተደንግጓል።
የወንጀል ህግ ወደ ኋላ ሄዶ አይሰራም ሲባል በመሰረታዊ ሕጉ ላይ ሁለት ዓይነት ውጤቶችን ያስከትላል፡፡ አንደኛው አንድ ድርጊት በሚፈፀምበት ጊዜ ድርጊቱ በጊዜው የማያስቀጣ ከነበረ ይኸው ድርጊት ከጊዜ በኋላ በወጣ ሕግ ወንጀል ነው ሊባል አይችልም፡፡ ሁለተኛው ድርጊቱ በተፈፀመበት ወቅት ወንጀል ቢሆንም እንኳን ወንጀለኛው መቀጣት ያለበት ድርጊቱ በተፈፀመበት ወቅት ተፈፃሚነት የነበረው የወንጀል ሕግ በደነገገው ጣሪያ መሆን አለበት የሚሉ ናቸው፡፡ ስለዚህም ከድርጊቱ በኋላ የወጣው ሕግ የቅጣት ጣሪያውን ከፍ ቢያደርገው ይህ ቅጣት ሕጉ ከመታወጁ በፊት ለተፈፀመ ወንጀል ተፈፃሚ መሆን የለበትም፡፡ ይሁንና አዲሱ ህግ ለተከሳሹ ወይም ለተቀጣው ሰው የሚጠቅም በሆነ ጊዜ ከድርጊቱ ኋላ የወጣው ህግ ተፈፃሚነት እንደሚኖረው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 22(3) ይደነግጋል። በተጨማሪ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 6 ስር እንደተደነገገው አዲሱ የወንጀል ህግ እንዲፀና ከተደረገ በኋላ አድራጊው ህጉ ከመፅናቱ በፊት ላደረገው ወንጀል ሲፈረድበት፣ ወንጀሉን በፈፀመበት ጊዜ በሥራ ላይ ከነበረው ሕግ ይልቅ ይሄኛው ሕግ ቅጣት የሚያቀልለት ሲሆን በአዲሱ ህግ ላይ የተመለከተው ቅጣት ይፈፀምበታል።
3. ለአንድ ጥፋት አንድ ቅጣት መርህ (Principle of Double Jeopardy)
የዚህ መርህ መሰረታዊ ሀሳብ ሰው በአንድ የወንጀል ድርጊት ክስ ቀርቦበት የመጨረሻ በሆነ ውሣኔ ጥፋተኝነቱ ተረጋግጦ በተቀጣበት ወይም በነፃ በተለቀቀበት ወንጀል እንደገና መከሰስና መቀጣት የለበትም የሚለው ነው፡፡ በዚህ መርህ ላይ አግባብነት ያላቸው የሕገ-መንግስቱና የወንጀል ሕጉ ድንጋጌዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡ የህገ-መንግስቱ አንቀፅ 23 “ማንኛውም ሰው በወንጀል ሕግና ሥነ-ሥርዓት መሰረት ተከሶ የመጨረሻ በሆነ ውሳኔ ጥፋተኝነቱ በተረጋገጠበት ወይም በነፃ በተለቀቀበት ወንጀል እንደገና አይከሰስም ወይም አይቀጣም” በማለት ሲደነግግ የወንጀል ሕጉም በአንቀፅ 2(5) ስር “ማንም ሰው በሕግ መሰረት የመጨረሻ በሆነ ውሳኔ ጥፋተኝነቱ ተረጋግጦ ከዚህ ቀደም በተቀጣበት ወይም ሌላ ሕጋዊ እርምጃ በተወሰደበት ወይም በነፃ በተለቀቀበት ወንጀል እንደገና አይከሰስም ወይም አይቀጣም” በማለት ደንግጓል፡፡
4. የእኩልነት መርህ (Principle of Equality)
Comments
Be the first to add a comment