የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
ሰላም!
አንዳንድ ቃላትን በተደጋጋሚ ስለምንጠቀምባቸው ብቻ ትርጓሜያቸውን የምናውቅ የሚመስለን ስንቶቻችን ነን? እስኪ ከዚህ በታች በደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 1065/2010 አንቀጽ 2 ንኡስ አንቀጽ 1 “ደን” ለሚለው ቃል የተሰጠውን ትርጓሜ እንመልከት!
“ደን” ማለት በደን መሬት፣ በመንገዶች ዳርቻ፣ በወንዝ ዳርቻ፣ በእርሻና የግጦሽ መሬቶች ውስጥና በዙሪያቸው እንዲሁም በመኖሪያ አካባቢዎችና ፓርኮች ውስጥ በተፈጥሮ የበቀሉ ወይም ተተክለው ወይም በሌላ ዘዴ የለሙ የዛፎችና የዕፅዋቶች እንዲሁም ሌሎች ብዝሃ-ሕይወቶች ክምችት ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ አንቀጽ ንኡሳን አንቀጾች 5፣ 6፣ 7፣ 8መሰረት ከባለቤትነት አንጻር ደን በ4 የሚከፈል ሲሆን እነርሱም፥-
“የመንግሥት ደን” ማለት በፌደራል እና በክልል መንግሥት ሥር የሚገኝ ማንኛውም ፍጹም ጥብቅ፣ ጥብቅ ወይም ምርት ሰጪ ደን ነው፤
“የግል ደን” ማለት የመንግስት እና የማህበረሰብ ያልሆነ በማንኛውም የግልና የተቋማት ይዞታ ላይ የሚገኝ ደን ነው፤
“የማሕበረሰብ ደን” ማለት የአንድ አካባቢ ህብረተሰብ የግል ወይም የወል ይዞታቸውን በጋራ በሚያወጡት ዕቅድ እና ሕገ-ደንብ መሠረት የለማ፣ የተጠበቀ፣ በጥቅም ላይ የሚውል እና የሚተዳደር ደን ነው፤
“የማሕበራት ደን” ማለት የደን አልሚዎች በማሕበር በመደራጀት የሚያለሙት፣ የሚጠብቁት፣ የሚጠቀሙበት እና የሚያስተዳድሩት ደን ነው፤
መስከረም 18 ቀን 2015 ኣ.ም
ፋሲካ አጌና (የሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት አቃቤ-ሕግ)
Comments
Be the first to add a comment