👉የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ ፕሮግራም በመጪው ማክሰኞ ይፋ ይደረጋል

🏷ለሚቀጥሉት 25 አመታት የሚተገበረው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ 2025 - 2050 ማስጀመሪያ ሀገራዊ ፕሮግራም (Construction Industry Transformation Initiative Launching Program) በመጪው ማክሰኞ ይካሄዳል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ቁልፍ ችግር በአጭር ጊዜ በመፍታት አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት እንዲያስችል ታስቦ በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የተቋቋመውና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችን እና የኢንዱስትሪውን ተዋናዮች በውስጡ ያቀፈው ዘጠኝ አባላት ያሉት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ስትሪንግ ኮሚቴ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ሥራውን በይፋ መጀመሩ ይታወቃል፡፡

በወቅቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሸቲቭ ስትሪንግ ኮሚቴ በተመሰረተበት ቀን ባደረገው ስብሰባ ላይ በስሩ ስድስትት የሥራ ቡድኖችን ያቋቋመ ሲሆን፤ ያቋቋማቸው የሥራ ቡድኖች በየራሳቸው የሠሯቸውን ሥራዎችና የደረሱበትን ደረጃ የሚገመግም መድረክ ሐሙስ፣ ነሐሴ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ቃሊቲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የስልጠና ማዕከል ውስጥ ተካሄዷል፡፡

በምስረታ መድረኩ ላይ ለተቋቋሙት የሥራ ቡድኖች በተሰጡ አቅጣጫዎች መሠረት የተቋቋሙት የሥራ ቡድኖች የሠሯቸውን ሥራዎች የተመለከቱ ሪፖርቶች በየቡድኑ ሰብሳቢዎች እንዲቀርቡ ከተደረገ በኋላ የጋራ ውይይት ተደርጎ ቀጣይ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ከሚንስቴር መ/ቤቱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ስብሰባውን የመሩትና የመግቢያ ንግግር ያደረጉት የስቲሪንግ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የመሠረተ-ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ የትምጌታ አስራት ናቸው።

በስብሰባውም መጨረሻ የስቲሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢው፣ ክቡር አቶ የትምጌታ አስራት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሸቲቭ 2025-2050 ነሐሴ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የኢንዱስትሪው ቤተሰቦች በተገኙበት በስካይላይት ሆቴል ይፋ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደሚታወቀው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለሀገር ልማት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑ ቢታወቅም ኢንዱስትሪው በአሁኑ ሰዓት ያሉበትን ችግሮች በተለመደው አስተሳሰብ እና አካሄድ ሊመቅረፍ ስለማይቻል የአተያይ እና የአካሄድ ለውጥ ማምጣት አስፈልጓል።

ከኢንደስትሪው ጋር የተያያዙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ እና ኢንዱስትሪው እንዲያድግ፣ አዲስ የተቋቋመው ስትሪንግ ኮሚቴ ከኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ካውንስል የሚሰጡ አቅጣጫዎችን በመውሰድ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ሥራውን የማስተባበር እና የመምራት ሚና እንዲጫወት ሥራውን በከፍተኛ ሀገራዊ ስሜት፣ በባለቤትነት እንዲያከናውን ከበላይ አመራሩ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የተዋቀረውን ስቲሪንግ ኮሚቴ ወደ ሥራ ለማስገባት የተጠራውን በመጀመሪያ ስብሰባ ወቅት ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እንደተናገሩት፦ ሥራውን በተቀናጀና ጥብቅ በሆነ የአመራር መርህ ማስኬድ የግድ መሆኑን ገልጸው በማንኛውም የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ የእርሳቸው ክትትልና ድጋፍ እንደማይለያቸው በማስታወስ የሥራውን ሂደት በቅርበት እንደሚከታተሉት ገልጸው ነበር፡፡

ስትሪንግ ኮሚቴው የሚመራባቸው አሳታፊ በሆነ መንገድ የተዘጋጁት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ሮድማፕ፤ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት ምዘና እና ዕውቅና ማዕቀፍ፤ እንዲሁም የኮንስትራክሽን ዘርፍ የአሠራር ማነቆን ለመገምገምና ለማሻሻል የሚረዱ Ease of Doing Business Framework in Construction Sector ሰነዶች ናቸው፡፡

በወቅቱ የስቲሪንግ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክቡር አቶ የትምጌታ አስራት የስቲሪንግ ኮሚቴውን የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ሲከፍቱ እንደተናገሩት፣ ኢንዱስትሪውን የመለወጥ ዕድል ለእኛ ስለተሰጠ ኢንዱስትሪውን በተሟላ ሁኔታ መለወጥ ይኖርብናል ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡

በ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ የሀገራችን 20 የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን በማሳደግ ወደ ውጭ ሀገር ሄደው በዘርፉ እንዲሰማሩ ግብ ተቀምጧል፡፡

ስለሆነም ዘጠኝ አባላት ያሉት ስቲሪንግ ኮሚቴ የተቋቋመው የተቀመጠውን ሀገራዊ አቅጣጫ በመከተል በፍጥነትና በጥራት ለውጥ የሚያመጣ ሥራ በመስራት ተወዳዳሪ የሆነ ኢንዱስትሪ ለመፍጠር ጉዞ መጀመሩን በማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ ተናግረው ነበር።

@etconp

Comments

Be the first to add a comment