👉የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት፥ ኖህ ሪልስቴት የ32 ቤት ገዢዎችን 24 አፓርታማ ቤቶች እንዳይሸጥ እግድ ጣለ❗️

በአዲስ አበባ ሴቶች አደባባይ በሚገኝ "ቪክትሪ ሳይት" የኖህ ሪልስቴት 32 ቤት ገዢዎች፥ ድርጅቱ በውሉ መሰረት ቤታችንን ስላላስረከበን ክስ ልንመሰርት በመሆኑ ክሱን እስክናቀርብ ቤቶች እንዳይሸጡ፣ እንዳይለወጡ እግድ ይሰጥልን በሚል ያቀረቡትን ቅድመ ክስ ችሎቱ ማጽናቱን የከሳሾች ጠበቃና የፍርድ ቤት ሰነድ አመለከቱ።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት ሰነድ፣ የእግድ ክስ እንዲሰጥ ነሐሴ 20/2018 ዓ/ም በገዢዎች መጠየቁን አያይዞ፣ ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድርጅቱ የ32 ቤት ገዢዎችን ቤቶች እንዳይሸጥ፣ እንዳይለውጥና ለሦስተኛ ወገን እንዳያስተላልፍ እግድ ማጽናቱን ያስረዳል።

የከሳሾች ጠበቃ አበበ ገብሩ አብርሃምና ጓደኞቹ የሕግ አገልግሎት ቢሮ ምን አለ?

የከሳሽ ጠበቆች ስድስት መሆናቸውን የገለጹት ከጠበቆች አንዱ፣ "የቅድመ ክስ ልናዘጋጅ ስለሆነ ድርጅቱ (ኖህ ሪልስቴት) የተሸጡ አፓርትመንቶችን ውል ሰርዞ ለሌላ ሦስተኛ ወገን ለማስተላለፍ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስለሰጠን እኛ ብንከስ ደግሞ ፍርድ ቤቱ ቢፈርድ ሊፈጸም የሚችልበት ንብረት ስለማይኖር ክሱን እስክናቀርብ የ60 ቀን እግድ ይሰጠን" በሚል ለፍ/ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱም ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ/ም የሚጠናቀቅ የ30 ቀን እግድ እንደሰጣቸው አስታውሰው፣ በዚህም 16 የሚለው ቅዳሜ እለት ስለነበር በቀን 20 ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት መደበኛ ክሱን እንዳቀረቡ ገልጸዋል።

"ችሎቱ የቀረበውን ክስ መሰረት አድርጎ ከዚህ ቀደም ተሰጥቶ የነበረው ጊዜያዊ እግድ ክርክሩ የመጨረሻ እልባት እስኪያገኝ ድረስ 32 ሰዎች የገዟቸው 24 ቤቶች እንዳይሸጡ፣ ለሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፉ እግድ ሰጥቷል" ብለዋል።

እግዱ ለሚመለከታቸው ተቋማትና ለኖህ ሪልስቴት እንዲደርስ መደረጉን ገልጸዋል። "አሁን የፍርድ ቤቶች የእረፍት ወቅት ስለሆነ በጥቅምት ችሎት እንደተጀመረ መደበኛ ክርክሩ ይቀጥላል" መባሉን ጠቁመዋል።

በጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱ ለኖህ መጥሪያ እንደላከ ገልጸው፣ "መጥሪያውን ፈርመው ተቀብለዋል፤ በዚያ ላይ የሰጡት መልስ፣ ለኛ የደረሰን ነገር የለም፤ ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።

ጉዳዩን በስምምነት ለመፍታት ለኖህ ሪልስቴት ቅድመ ማስጠንቀቂያ መሰጡን ተናግረዋል።

"ችግሩ በውይይት እንዲፈታ የ15 ቀናት ማስጠንቀቂያ በውሉ መሰረት ተሰጥቶ ነበር፤ ድርጅቱ ማስጠንቀቂያውን ተቀብሎ ምላሽ አልሰጠም፤ የሰጠው ምላሽ 'የጠበቆች ማንነት የሚገልጽ ነገር ላኩልን' የሚል ነው፤ ይህንም የላኩት ቅድመ ማስጠንቀቂያው በ15 ሊያበቃ በ14 ነው። ይህ የሚያመላክተው ጉዳዩን በድርድር ለፍታት ፍላጎት እንደሌላቸው ነው" ብለዋል።

Via ቲክቫህ ኢትዮጵያ

@etconp

Comments

Be the first to add a comment