የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
የፍትህሐብሔር ስነ-ስርዓት ሕግ
በአገራችን የሰዎችን መብትና ግዴታዎች ዘርዝረዉ የሚያቀርቡ እና ሌላዉ ደግሞ መብቶችና ግዴታዎች እንዴት ወደ ስራ እንደሚገቡ ስነ-ስርዓቱን የሚደነግጉ ሕጎች አሉ። እንደ የፍትሐብሔር ሕግ(በዉስጡ የዉርስ፣የንብረት፣የዉል፣የዉክልና የምሳስሉትን ሕጎች የያዘ ነዉ)፣የቤተሰብ ሕግ፣የወንጀል ህግ ያሉት የሰዎችን መብትና ግዴታዎች ዘርዝረዉ የሚያስቀምጡ ሲሆኑ እንደ የፍትህሐብሔር ስነ-ስርዓት ሕግ፣ የወንጀል ስነ-ስርዓት ሕግ እና የመሳሰሉት ደግሞ የስነስርዓት ህጎች ናቸዉ። እነዚህ የስነ-ስርዓት ህጎች አንድ ሰዉ በህጉ ያገኛቸዉን መብትና ጥቅሞች ማስከበር ሲፈልግ የሚከተላቸዉን መንገዶች ዘርዝሮ የሚያስቀምጥ ነዉ።
ከስነ-ስርዓት ህጎች አንዱ የሆነዉም የፍትህሐብሔር ስነ-ስርዓት ሕግ ሲሆን በዉስጡም የፍትሐብሔር ክርክር ማንሳት የሚፈልግ ሰዉ (ተፈጥሮአዊ ሆነ በህግ ሰዉነት የተሰጠዉ) ከክስ አመሰራረት አንስቶ ፍርድ ቤት ዉስጥ የሚካሄዱ ሰነስርዓቶችን፣ የፍርድ ቤት ስልጣን፣ የይግባኝ አቀራረብ፣ እግድ አሰጣጥ፣ የተከራካሪ ወገኖች መብት ማለፊያ መንገዶች እያሉ የሚቀጥሉ አካሄዶችን እንዴት መከተል እንዳለበት የሚያሳይ ህጋችን ነዉ። በሌላ ጎኑ ደግሞ ዳኞች የፍትሐብሔር ክርክሮችን እንዴት መምራት እንዳልባቸው እና ትእዛዝ፣ብይን እና ፍርድ ምን አይነት ስርአት ተከትለዉ እንዴት መስጠት እንዳለባቸዉ የሚያሳዩ አንቀጻት የያዘ ነዉ።
በመሆኑም ክርክር ማቅረብ የሚፈልግ ሰዉ በመጀመሪያ ማስረጃዎቹን ካሰባሰበ በኋላ በፍትህሐብሔር ስነ-ስርዓት ሕግ (የፍ/ስ/ስ/ህ/) አንቀጽ 222 እና 223 መሰረት ክሱን አዘጋጅቶ ለፍርድ ቤት በማቅረብ ቀጠሮ በማስያዝ ለተከሳሽ መጥሪያ በአግባቡ ማድረስ ይጠበቅበታል። በአግባቡ መጥሪያ ደርሶት ችሎት ቀርቦ ክርክሩን ያላሰማም ተከሳሽ ጉዳዩ በሌለበት እንዲቀጠል ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ይሰጣል። ተከሳሹ መጥሪያ ደርሶት ከቀረበም በጽሁፍ መልሱን እንዲያቀርብ ይደረጋል ነገር ግን ማስገደድ አይቻልም። ቀጣዩ ሂደትም የሚሆነዉ ክስ መስማት ነዉ። ክስ ለመስማት በተቀጠረበትም ቀን ተከሳሽ ካልቀረበ ክርክሩ በሌለበት እንዲሰማ የሚደረግ ሲሆን ከሳሽ ካልቀረበ ደግሞ መዝገቡ ይዘጋል። ከሳሽ ባይቀርብም እንኳን ተከሳሽ ከቀረበበት ክስ ያመነዉ ካለ ፍርድ ቤቱ በታመነዉ ልክ ዉሳኔ መስጠት እንዳለበት የፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 73 ይደነግጋል። ግራቀኝ ቀርበዉ ክርክራቸዉን ካሰሙ ግን ፍርድ ቤቱ ለጉዳዩ አግባብነት ያለዉን ጭብጥ መስርቶ እነዚህን ጭብጦች ሊያስረዱ የሚችሉ ማስረጃዎች የሰነድም ይሁን የሰዉ እንዲቀርቡ ያደርጋል። በመጨረሻም አግባብነት ያለዉ ዉሳኔ ወይም ብይን ይሰጣል።
የችሎቱ አመራር በአጭሩ ከላይ የተቀመጠዉ ሲሆን ስለ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ የተወሰነ ልበላችሁ። የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ማለት ፍርድ ቤቱ ወደ ፍሬ ነገር ክርክር መግባት ሳያስፈልገዉ መዝገቡን መዝጋት የሚያስችለው የስነስርዓት ሂደት ነዉ። ይህም መቃወሚያ በራሱ በፍርድ ቤቱ ተነሳሽነት ወይም በተከሳሽ በኩል ሊነሳ ይችላል። የፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 244 ላይም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ሆነው ሊቅርቡ የሚችሉትን ዘርዝሮ አስቀጧምል። እነዚህ መቃወሚያዎች ፍርድ ቤትም ሆነ ተከራካሪ ወገኖች ግዜያቸዉንም ሆነ ጉልበታቸዉን ያላግባብ ሳያባክኑ ጉዳዩ በአጭሩ የሚያልቅበትን መንገድ የሚፈጥሩ በመሆናቸዉ ጥቅማቸዉ ቀላል የሚባል አይደለም። በመቃወሚያነት ሊቀርቡ ከሚችሉ ነጥቦች መካከልም ይርጋ፣ከዚህ በፊት በሌላ መዝገብ ክርክር ተደርጎበት ዉሳኔ ያረፈበት ከሆነ ወይም በሌላ መዝገብ በመታየት ላይ ከሆነ፣ በእርቅ ያለቀ ጉዳይ፣ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን ከሌለዉ የመሳሰሉት ናቸዉ።
የፍትህሐብሔር ስነ-ስርዓት ሕግ እንዲህ በአጭር ጽሁፍ ቀርቶ በመድብል እንኳን ቢጽፉት ሁሌም አዲስ ጉዳይ የማይጠፋዉ ሰፊ እና ሳቢ የሆነ ክፍል በመሆኑ ከብዙ በትንሹ አልኳችሁ።
የቦሌ/ክ/ከ/ህ/ስ/የህ/ም ዳይሬክቶሬት
ዐ/ህግ ዉብአለም መስፍን
Comments
Be the first to add a comment