👉ውል ከተፈራረሙ በኋላ ጨረታ ሊሰረዝ ይችላልን?

👋ሰላም ጤና ይስጥልን እንደምን አላችሁ? አንድ የቻናላችን ቤተሰብ "ድርጅታችን በ egp ተወዳድሮ ጨረታ ከአሸነፈ በኋላ በግለሰቦች ጣልቃ ገብነት እስከ ቦርድ ደርሶ በጨረታው ሒደት ምንም ችግር እንደሌለበት ተረጋግጦ ውል ከገባን እና የጨረታ ማስከበሪያ ከአስያዝን በኋላ ከስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና በሰጠን ምክረ ሀሳብ መሠረት ጨረታውን ሠርዘናል ብሎ በግልባጭ ምንም ሳያማክረን ገለጸልን። ለመሆኑ በቅድሚያ ውሉን አሰሪ ስለሆነ ብቻ በራሱ መሠረዝ ይችላል ወይ?" የሚል ጥያቄ አርበዋል።

📌እኛም የጋራ ሀሳብ ይሆነን ዘንድ በዚህ ቻናል ላይ አቅርበንዋል።

📍በኮንስትራክሽን የጨረታ ሂደት ውስጥ ሦስት አይነት ዋና ዋና ሰነዶች የሚኖሩበትን ሂደት የሚያልፍ ነው። ይኸውም የመጀመሪያው አሠሪው አካል (employer/client/public body)  የሚባለው አካል የሚያዘጋጀው ስለፕሮጀክቱ ዝርዝር ይዘት፣ ስለተጫራቾች መመሪያ፣ ስለተጫራጮች ተጠባቂ አቅም እና ስለሥራዎች ዝርዝር ልኬትና ንድፍ የሚያስረዳ   ተጫራቾች የማይመለስ የሰነድ መግዢያ ከፍለው የሚገዙት ሰነድ ሲሆን የጨረታ ሰነድ (Tender or Bid Document) ይባላል። ሁለተኛው ሰነድ ተጫራቾች (Bidders) በጨረታ ሰነዱ መስፈርትና ልኬት መሰረት ያላቸውን ቴኪኒካዊ ማሙላት እና የግንባታ ዋጋ የሚያረጋግጡ ልዩ ልዩ ይዘቶችን የያዘ በተቋራጩ ማኅተም የተረጋገጠ ለአሰሪው አካል የሚገባ የጨረታ ምላሽ ሰነድ (Bid Response Document)  ነው። ሦስተኛው ሰነድ አሠሪው አካል ከተሰበሰቡት የተጫራቾች ሰነዶች መካከል በውድድር አሳልፎ ከመረጠው ተጫራች ጋር የሚፈጽመው የግንባታ ውል ሰነድ (Contract Document) ይባላል።

በዚህ ይዘት የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ሰነዶች ጠቅላላ ሂደታቸው እስኪጠናቀቁ ድረስ ያለው ሂደት የጨረታ ጊዜ (ወቅት) ይባላል። ይህ ጊዜ በውድድሩ ሰዓት ቅሬታ ካለ ቅሬታው እስኪፈታ ድረስ ያለውን ስለሚያጠቃልል የቀረበው ቅሬታ በሙሉ ታይቶና ተገምግሞ የመጨረሻ አሸናፊ የሆነው አካል ውል እንዲፈርም እስከሚደረግበት ጊዜ ድረስ ያለው ያጠቃልላል። በጨረታ ጊዜ ውስጥ ባለው በማንኛውም ሰዓት አሠሪው አካል ጨረታውን የሚሰርዝበት ምክንያት ወይም ሕጋዊ አስገዳጅነት ወይም የተሻለ አማራጭ ካገኘ የመሰረዝ መብቱ ሙሉ ለሙሉ የተጠበቀ እስከመሆን ድረስ መብት ይኖረዋል።

ነገር ግን የጨረታ ጊዜ ተጠናቆ አሠሪው አካል ከተቋራጩ ጋር የሥራ (የግንባታ ወይም የማማከር ወይም የዲዛይን) አገልግሎት እንዲሰጠው ውል ከተፈራረመ በኋላ የውሉ ጉዳይ የጋራ ጉዳይ እንጂ የአንደኛው አካል ፍላጎትን ብቻ የሚተገብር አይሆንም። የሥራ ውል (Contract of Works) ውል ስለሚቋረጥባቸው ምክንያቶችም በዝርዝር የሚገልጽ ይዘት ያለው ስለሆነ ውል ሊቋረጥ የሚችለው በዚያ የውል ሁኔታ Contract Condition) መሰረት እንጂ ከዚያ ውጪ ከሆነ ለተጎጂው አካል ወይም ውል የሚቋረጥበት አካል ውል የማቋረጥ ፍላጎት ካሳየው አካል አስፈላጊውን ክፍያ ሊጠይቅ ይችላል። ውል ስለሚፈርስባቸው ምክንያቶች የሀገራችን የመንግሥት ግዢ እና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ (PPPAA) ጠቅላላ ድንጋጌ አንቀጽ 21 (General Condition of Contract, Clause 21) ሥር ባሉት ሁኔታዎች ላይ ይመሰረታል። ውል ለመሰረዝም ሊከተላቸው የሚገቡ ቅደም ተከተሎች እና ፕሮቶኮሎች እንዳሉ በዚህ ድንጋጌ ላይ ተወስኗል።

በመንግሥት ግዢ መመሪያ ከተገለጸው በተጨማሪ ከውል ሁኔታዎች በተጨማሪ የሀገራችን የፍትሐ ብሔር ሕግ (Ethiopia Civil Code) ውል የመሰረዝ ሀሳብን ማንሳት ለማንኛውም ወገን የተፈቀደ ሲሆን በአንቀጽ 3055 ሥር በተገለጸው መሰረት አሰሪው አካል ሥራ ተቋራጩ አንዳችም ጥፋት ባይፈጽምም እንኳን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የፈረመውን ውል የማፍረስ መብት ተሰጥቶታል። ነገር ግን በቁጥር 3036 እንደተገለጸው ሥራ ተቋራጩ የውሉን ጅምላ ዋጋ (በተለይ ለላምፕ ሰም ውል) ወይም አቅራቢያ ዋጋ የማግኘት መብት ያለው ሲሆን ሥራ ተቋራጩ ከማውጣት የቀረለትን ወጪ ተቀናሽ ማድረግ አለበት። ቢሆንም ግን አቅራቢያ በሆነ ግምት ተሰልቶ እንደሆነ አሠሪው መክፈል ያለበትን ገንዘብ እስከ 20% ድረስ በመጨመር ሥራ ተቋራጩ ሊጠይቅ ይችላል" ተብሎ ተደንግጓል።

በመሆኑም አንድ አሠሪ አካል ሼል ተቋራጩ አሸናፊ መሆኑን ገልጾ ውል እንዲፈርም ካደረገ በኋላ በውል ሰነዱ ውስጥ ከተጠቀሱ ወይም በሌሎች ቅቡል የሕግ ማእቀፎች የተደነገጉ ምክንያቶች ካልሆነ በቀር በማንኛውም ጊዜ ውል የማፍረስ መብት የለው። ውል ማፍረስ እና ጨረታ መዘረዝ በእጅጉ የሚለያዩ ናቸው። ነገር ግን ውል የማቋረጥ ፍላጎት ካለው ስለማይከለከል ሼል ተቋራጩ በውል አፈጻጸም ሂደት ላባከናቸው ወጪዎች (ለምሳሌ፦ የሥራ ማስጀመሪያ ቦንድ ገንዘብ ወለድ፣ የውል ማስከበሪያ ወለድ፣ የብቃት ማስያዢያ ቦንድ ወለድ፣ በውል አፈጻጸም ሂደት ላወጣቸው የትራንስፖርት፣ የስቴሽነሪ፣ ለተጀመሩ የሥራ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ክፍያ ... ) ወጪዎች የመጠየቅም መብት ይኖረዋል። 

@etconp

1 comment

በመጀመሪያ ደረጃ ውለታ ሰነድ ከተፈረመ በኋላ ጨረታ ተሰረዘ ተብሎ አይነገርም በተጨማሪም ውል ሲፈረም የጨረታ ማስከበሪያ በውል ማስከበሪያ ይተካል እንጅ ....የጨረታ ማስከበሪያ ካስያዝን በኋላ ተብሎ አይጠቀስም። ስለሆነም ውል ተቋረጠ እንጅ ጨረታ ተሰረዝ የሚለው ሐሳብ አይገልፀውም። በመኾኑም ውል ማቋረጫ ምክንያቶች መሠረት የተደረጉ ካሉ ልዩ የውል ኹኔታው ላይ አይቶ አቤቱታ ማቅረብ የሚቻል ይኾናል።