ሰላም ለሁላችን!
በ1954 ወጥቶ እስከዛሬም ድረስ በስራ ላይ በሚገኘው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነስርዓት ፖሊስ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተጠርጣሪን መያዝ የሚችልባቸው ምክንያቶች በሕግ ቁጥር 51 እንዲህ የተዘረዘሩት ናቸው፡፡
1. ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ የፖሊስ ሠራዊት ባልደረባ መያዝ የሚችለው
(ሀ) ከአንድ ዓመት በማያንስ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ለመሥራት ዝግጁ የሆነውን ወይም ሠርቷል ተብሎ በሚገባ የተጠረጠረውን ሰው
(ለ) የሕዝብን ጸጥታ በማበላሸት ላይ የሚገኘውን ሰው
(ሐ) የፖሊስ ሠራዊት ባልደረባ ሥራውን በሚፈጽምበት ጊዜ ተቃዋሚነትን በማሳየት የሚከላከለውን ወይም በሕግ ከታሰረበት የሚያመልጠውን ወይም ለማምለጥ የሚሞክረውን ሰው፤
(መ) ከፖሊስ ተጠባባቂነት የሚያመልጥ ወይም አምልጦ የሄደ ለመሆኑ በሚገባ የሚጠረጠረውን ሰው፤
(ሠ) ከወታደርነት ወይም ከፖሊስ ሠራዊት ከድቶ የሄደ ለመሆኑ በሚገባ የሚጠረጠረውን ሰው፤
(ረ) ሕግ የማይፈቅድለትን የቤት መሠርሠሪያ ወይም ቤትን ሰብሮ መግቢያ መሣሪያ የተገኘበት ሰው፤
(ሰ) ሕግ የማይፈቅድለትን የተሰረቀ ዕቃ የያዘ ለመሆኑ በሚገባ የሚያስጠረጥር ሆኖ ወይም ወንጀል በመፈጸም ረገድ ያገኘው ዕቃ በይዞታው የተገኘበት ሰው፤
(ሸ) በወንጀል ሕግ አንቀጽ 477 እንደተመለከትነው አደገኛ ሥራ ፈት መሆኑ በሚገባ የሚጠረጠረውን ሰው ነው።
2. የመንግሥት ባለሥልጣን ሠራተኞች ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ሰውን ለመያዝ በሌላ በልዩ ሕግ የሚሰጣቸው ሥልጣን የተጠበቀ ነው።
ለሰላምና ለሕግ የበላይነት የድርሻችንን መወጣትን አንርሳ!!!
ቸር ይግጠመን
ሲሳይ ሰማኝ የካቲት (7/6/14 ዓ.ም)

Comments

Be the first to add a comment