ሰላም ጤና ይስጥልኝ
ከተማችንን ጽዱና ለኑሮ የተመቸች ከሚያደርጓት ዋነኛ ነገሮች አንዱ የከተማዋን ጽዳት መጠበቅ ሲሆን ለዚህ ደግሞ በጽዳት ስራ ላይ ከተሰማሩት ባለፈ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚመለከት ስለሚሆን ከደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አሰባሰብ እና አወጋገድን በተመለከተ ከወጡ ሕጎች የተወሰኑትን እንመለከታለን መልካም ንባብ
ደረቅ ቆሻሻ ምን ማለት ነዉ ስንት ዓይነት ደረቅ ቆሻሻ አለ?
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሸሻለ የተቀናጀ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ደንብ ቁጥር 100/2010 አንቀጽ 1 (7)፤ (8)፤ (9)፤ (10)
የደረቅ ቆሻሻ ተርጓሜ፡- ከመኖሪያ ቤት፤ ከንግድ፤ ከኢንዱስትሪ፤ ከተለያዩ ተቋማት፤ ከጋራዥ፤ ከመንገድ ጽዳት፤ ከግብርና፤ ከእንስሳትና በጠቅላላዉ ከህብረተሰቡ ስራዎች ምክንያት የሚፈጠር ጥቅም የማይሰጥ ወይም የማይፈለግ ተብሎ ሚጣል ጠጣር/ከፊል ጠጣር የሆነ ቁስ ነዉ፡፡
ጥቃቅን ደረቅ ቆሻሻ፡- በየቦታዉ በግልጽ የሚታዩና በሰዎች እንቅስቃሴ ምክንያት ተጠቃሚዎች የሚጥሏቸዉ የሲጋራ ቁርጥራጭ፤ የሶፍት ወረቀት፤ ፌስታል፤ የጫት ገረባ፤ የፍራፍሬ ተረፈ-ምርቶች ትራንስፖርት ቲኬት፤ ሞባይል ካርዶች፤ የማስቲካና ከረሜላ ሽፋኖች፤…… የሚያጠቃልል ነዉ፡፡
ኤልክትሮኒክስ ነክ ቆሻሻዎች፡- እንደገና አገልግሎት ሊሰጡ ወይም ላይሰጡ ሚችሉ ኮምፕዩተሮች፤ ፎቶ ኮፒ ማሽኖች፤ ማንናዉም የስልክ ቀፎ፤ ቴሌቪዥኖች፤ የማቀዝቀዣ መሳሪያዎች፤ ….. እና የእነዚህ ዕቃዎች የዉስጥና የዉጭ ስብርባሪና የወላለቁ አካላት ማለት ነዉ፡፡
አደገኛ ደረቅ ቆሻሻ፡- የሚፈነዱ፤ በቀላሉ በእሳት የሚቀጣጠሉ፤ መርዛማ ነገሮች፤ ራዲዮአክሪቭ ቁሶች፤ ልዩ ልዩ ኬሚካሎች፤ የደም ንክኪ ያላቸዉ ሆነዉ ከኢንዱስትሪ፤ ከማምረቻ፤ ከጤና ተቋማት እና ከቤተ ሙከራ የሚወጡና በሰዉ፤ በእንስሳ፤ በእጽዋትና በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ማንኛዉም ቆሻሻ ነዉ፡፡

ህድአት ጌታቸዉ
ህዳር/2014 ዓ.ም

Comments

Be the first to add a comment