ክፍል 2 ስለ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አመራር እና ኃላፊነት ወሰን፣
ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እንደ ማንኛውም ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊኖረው ግዴታ ሲሆን ፤ አባሉ ራሱ ወይም ሌላ ሰው የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ሊሆን ይችላል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ አንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ በህግ የተሠጠው ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
አባሉ በንግድ ሕጉ ለአንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጠቅላላ ጉባዬ የተሠጠው ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ አባሉ በጠቅላላ ጉባዔ ሥልጣኑ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ቃለጉባዔ ስበሰባው በተደረገ ከሦስት ሣምንታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በፅሁፍ ተዘጋጅተው የማህበር ማህደሩ ውስጥ ሊቀመጡ እንዲሁም ውሳኔዎቹ የማህበሩን ማቋቋሚያ መግለጫ የሚለውጡ ከሆነ ውሳኔው ከተሠጠበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በንግድ መዝገብ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ይህን ቅድመ ሁኔታ ባይሟላ እንኳን ውሳኔዎቹ በሕግ የሚፀኑ ቢሆንም ጉድለቱ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት አባሉና ማህበሩ በአንድነት እና በተናጠል ተጠያቂዎች ናቸው
ምንም እንኳን የአባሉ ኃላፊነት የተወሰነ (Limited Liability) ቢሆንም አባሉ ወይም በማህበሩ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቁጥጥር ያለው ሌላ ሰው ማህበሩን፣ ወይም የማህበሩን ገንዘብ ጠያቂዎች ጉዳት ላይ የሚጥል ሕገ ወጥ ድርጊት ሆን ብሎ ከፈፀመ፤ የማህበሩን ንብረትን ከራሱ ንብረት ጋር ከቀላቀለ፤ የማህበሩን እና የራሱን ማንነት ካልነጣጠለ፤ ስለማህበሩ የፋይናንስ አቋም የማህበሩን ገንዘብ ጠያቂዎች ሊያሳስት የሚችል መረጃ ሆን ብሎ ካወጣ፤ ያለ ተመጣጣኝ ክፍያ የማህበሩን ሀብት ለራሱ ወይም ለሦስተኛ ወገኖች የግል ጥቅም ካዋለ፤ በሕግ ሊከፈል ከሚችለው በላይ የትርፍ ክፍያ ከፈፀመ ወይም ተመሳሳይ ተግባራት ከፈፀመ ከማህበሩ ጋር በአንድነት እና በተናጠል ተጠያቂ ይሆናል ወይም በሌላ አገላለፅ የኩባንያን ጭምብል መግለጥ መርህ ወይም piercing the corporate veil principle ተግባራዊ ይሆናል፡፡
ስለማህበሩ መፍረስ፣
ስለ ማህበራት መፍረስ ከተጠቀሱት ጠቅላላ ድንጋጌዎች በተጨማሪ አባሉ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሂሳቡ ሳይጣራ እንዲፈርስ ከፈለገ ሂሳብ ሳይጣራ ሊፈርስ ይችላል፡፡ ማህበሩ ሂሳቡ ሳይጣራ የፈረሰ እንደሆነ የማህበሩ ሃብት በጠቅላላው ለአባሉ ይተላለፋል፡፡ በማናቸውም ምክንያት ማህበሩ ከፈረሰ በኋላ ገንዘብ ጠያቂዎች የቀረቡ እንደሆነ አባሉ በግሉ ተጠያቂ ይሆናል፡፡
ማህበሩ ከፈረሰ በኃላ የሚቀርብ ገንዘብ ጠያቂ የሚያቀርበው ጥያቄ ማህበሩ መፍረሱን ካወቀ በአምስት ዓመት ወይም የማህበሩ ሀብት ለአባሉ ከተከፋፈለ በምንም ዓይነት ከአስር ዓመት በኋላ ሊቀርብ አይችልም፡፡
ከላይ በዝርዝር ከተመለከትናቸው ነጥቦች ውጪ ስለ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተደነገጉት ህጎች ለባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርም የሚያገለግሉ በመሆኑ ክፍተቶችን ለመሙላት ልንጠቀምባቸው እንችላለን፡፡
ኦምኒኤል (12/02/2014 ዓ.ም)

Comments

Be the first to add a comment