👉አሜሪካ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክትን እንደምትደግፍ በይፋ አስታወቀች

💫በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ያለውን ጫና ለማርገብና የአገሪቱን የረዥም ጊዜ የአቪዬሽን ዕድገት የማስጠበቅ ዓላማ ላለውና በኦሮሚያ ክልል በቢሾፍቱ በአሥር ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለሚገነባው ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ፕሮጀክት፣ አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ በይፋ መግለጽዋን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቡሎስ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ዶ/ር) ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስና ሌሎች ተቋማትም ፕሮጀክቱን እየደገፉት ነው፡፡

አማካሪው መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም. ይፋ በተደረገ መግለጫቸው፣ ‹‹ከኢትዮጵያ በቀጥታ ወደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ተመለስኩ፡፡ ለአዲሱ የኤርፖርት ፕሮጀክት ስለምናደርገው ድጋፍ ተነጋግረንበታል። ይህ ኤርፖርት ምናልባትም በአፍሪካ ትልቁ አውሮፕላን ማረፊያ የሚሆን ሲሆን፣ በዓለም ላይ ካሉት ትልልቅ ኤርፖርቶችም አንዱ ይሆናል። አሥር ቢሊዮን ዶላር ምናልባትም የበለጠ ገንዘብ የሚፈልግ ፕሮጀክት ነው፤›› ብለዋል።

የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪው ቡሎስ፣ ‹‹የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ፕሮጀክት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔና ሌሎች ተቋማት እየደገፉት ነው፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር የአፍሪካ ፖሊሲ ውጤት ማሳየት ጀምሯል ያሉት አማካሪው፣ ከዕርዳታ ወደ ንግድ በመሸጋገር የንግድ ሽርክናዎችን በማጎልበት ላይ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

‹‹ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከዕርዳታ ወደ ንግድ እየተሸጋገረ ያለውን የአፍሪካ ፖሊሲያቸውን በአኅጉሪቱ ውስጥ ጠንካራ አጋርነት በመፍጠርና በመደገፍ ላይ ይገኛሉ፤›› ብለዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ ቡሎስ፣ ‹‹ከቦይንግ ጋር በተያያዙ ከበርካታ ፕሮጀክቶች ጋር ተቀራርበን እየሠራን ነው፡፡ ቦይንግ እንደምናውቀው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ትብብር ያለው ሲሆን፣ ሌሎችም ብዙ መሰል አጋርነቶች አሉት፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ከሁለት ሳምንታት ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ፕሮጀክትን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ባካሄደው የባለድርሻ አካላት ውይይት፣ የግንባታ ፕሮጀክቱን ዝርዝር የፋይናንስና የአሠራር አወቃቀሮችን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፣ የአየር መንገድ ግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰውና በውይይቱ ላይ የቀረቡት ሰነዶች ለፕሮጀክቱ የፋይናንስ ምንጮች ይሆናሉ በሚል የሚጠበቁት ከኮሪያ፣ ከጃፓን፣ ከቱርኪዬ፣ ከእንግሊዝ፣ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከቻይናና ከሌሎች ያልተገለጹ መዳረሻዎችና ምንጮች መሆናቸውን ይጠቁማሉ።

የኤርፖርት ፕሮጀክቱ በገንዘብ የሚደገፍበትን (Financing) የሚያብራራው ዕቅዱ ዋነኛው በሥራ ላይ የሚያውለው የኢንጂነሪንግ፣ የግዥና የኮንስትራክሽን (ኢፒሲ) ተቋራጭ የሚመራ የኤክስፖርት ብድር ኤጀንሲ (ECA) የፋይናንስ ሞዴል መሆኑን ያሳያል። በዚህ አካሄድ የኢንጂነሪንግ፣ የግዥና የኮንስትራክሽን ኮንትራክተሮች የጨረታው አካል ሆነው ከኤክስፖርት ብድር ኤጀንሲ ጋር ቁርኝነት ያላቸው የፋይናንስ ፓኬጆችን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። የግምገማ መሥፈርቶች የግንባታ ወጪዎች 70 በመቶ፣ 3ዐ በመቶ በፋይናንስ ወጪዎች ላይ መሠረት በማድረግ ይወሰናሉ። ይህ ሥርዓት ጥራትን ከአስተማማኝ የፋይናንስ ሥርዓት ጋር ለማስተሳሰር ታልሞ የተበጀ መሆኑም ተገልጿል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሾመው የፋይናንስ አማካሪና የኤክስፖርት ብድር ኤጀንሲውን የሚያስተባብሩ ባንኮች የቴክኒክ መመዘኛዎቹን እንደሚወስኑም ተብራርቷል።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ባለቤትነት የተያዘና ለዚህ ሲባል በሚቋቋም ልዩ ኩባንያ ሥር እንደሚተዳደር እንደሚደረግም ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ሁሉንም የፕሮጀክቱን የገንዘብ አስተዳደር በዚሁ ኩባንያ ሥር በማድረግ ለገንዘብ አቅራቢዎችና አጋሮች የፕሮጀክቱን የፋይናንስ ነፃነትና ግልጽነት ያረጋግጣል በሚል በመታመኑ የተደረገ መሆኑም ተጠቅሷል።

የቢሾፍቱ ሜጋ ኤርፖርት 27ዐ አውሮፕላኖችን በአንዴ ማቆም እንደሚያስችል፣ እንዲሁም የአየር መንገድ ግሩፑን የካርቦን ልቀት በ15 በመቶ እንደሚቀንስ፣ በዓመት 3.7 ሚሊዮን ቶን ጭነት የማጓጓዝ አቅም እንደሚኖረውና አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ዕጩ አሥር ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን መገለጹን መዘገባችን ይታወሳል።

ኤርፖርቱ በአጠቃላይ አንድ ትልቅ ተርሚናል፣ ከ27ዐ በላይ አውሮፕላኖች ማቆም የሚያስችል የአውሮፕላን ማረፊያ ሥፍራ፣ አራት የአውሮፕላን መንደርደሪያ ሥፍራዎችን፣ አዲሱን የኤርፖርት ከተማ በቀጥታ ከአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት ጋር የሚያገናኝ ፈጣን የባቡር መንገድ፣ ፈጣን የአስፋልት መንገድ፣ የአውሮፕላን ጥገና ክፍሎች፣ ካርጎና ሌሎችም ተጨማሪ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችንም እንደሚያካትት ተገልጿል።

የመጀመሪያው ክፍል ግንባታ በሁለት የአውሮፕላን መንደርደሪያዎችና ሌሎች መሠረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናቆ እ.ኤ.አ. በኅዳር ወር 2029 ሥራ እንዲጀምር እንደሚጠበቅ፣ በመጀመሪያ ምዕራፍ በሚከናወነው ግንባታ ብቻ በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን እንደሚያስተናግድ ተነግሯል።

Via ኢንፍራኮን ሚዲያን


@etconp

Comments

Be the first to add a comment