የአለማቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብት ጥበቃ ስምምነትና ኢትዮጵያ፡- ክፍል አንድ
መግቢያ

የዚህ ስምምነት ዓላማ መላ አካል ጉዳተኞች በሁሉም ዓይነት ሰብአዊ መብቶችና መሠረታዊ ነፃነቶች ረገድ ሙሉና እኩል ተጠቃሚነት ያላቸው ስለመሆኑ ማረጋገጥ፣ ማሳደግና ለነዚሁ ጥበቃ ማድረግ፣ ብሎም ተፈጥሮአዊ ክብራቸውን ከፍ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ከተዋዋይ ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ይኽንን ስምምነት በአዋጅቁጥር 676/2002 በማጽደቅ በህገመንግስቱ አንቀጽ 9/4 መሰረት የራሷ የህግ ክፍል ያደረገችው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በዚህ ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ ምን እንዳደረገች በተለይም ከህግ ማውጣትና አፈጻጸም ጋር በራሱ በስምምነቱ አንቀጾች በመመስረት ምጥን ዳሰሳ ማድረግ የዚች መጣጥፍ መነሻና መድረሻ ነው፡፡
አንቀጽ 4 አለማዳላት የሚል ርዕስ ሲኖረው፣
ሀገራት በፖሊሲ፣ በህግና በሌሎችም ስራዎች አካል ጉዳተኞችን የሚያካትቱ እንዲሆኑ ይልቁንም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አግላይ ስራዎች እንዳይሰሩ ተሰርተው ቢገኙም እርማት ለመውሰድ ስምምነት ገብተዋል፡፡ የሀገራችንም ትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው፣ አካል ጉዳተኞች ትኩረት እንዲሰጣቸው ቢደነግግም ባለፈው የ2012 የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ደረጃ ገብተው የሚገኙት 11 ፐርሰንቱ ብቻ ሲሆኑ የትምህርቱ ደረጃ ከፍ እያለበሄደ መጠን ቁጥሩ እየቀነሰ ይሄዳል፡፡
ተከታዩ አንቀጽ 9 ተደራሽነትን የሚመለከት ነው፡፡
አካል ጉዳተኞች ኑሯቸውን በነፃነት እንዲመሩና በየትኛውም የሕይወት መስክ ያልተገደበ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል ተዋዋይ መንግሥታት እነዚሁ ወገኖች ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር ባልተናነሰ ሁኔታ ቁሳዊ አካባቢን የመድረስም ሆነ በመጓጓዣ ዘዴዎች፣ የመረጃና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችንና ስርዓቶችን ጨምሮ በመረጃና መገናኛ አውታሮች እንዲሁም በከተማም ይሁን በገጠር ለሕዝብ ክፍት በተደረጉ ተቋማትና አገልግሎቶች የመጠቀም ዕድል የተመቻቸላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ተገቢነት ያላቸውን እርምጃዎች ይወስዳሉ፡፡
በተደራሽነት ላይ የተጋረጡትን መሰናክሎችና ገደቦች መለየትና ማስወገድን የሚያጠቃልሉት እነዚህ እርምጃዎች ከሁሉ በፊት ቀጥሎ በተመለከቱት ላይ ተፈፃሚዎች ይሆናሉ፡
ሀ) ሕንፃዎች፣ መንገዶች፣ የመጓጓዣ ዘዴዎችና እንደ ትምህርት ቤቶች፣ የመኖሪያ ሥፍራዎች፣ የሕክምና አገልግሎት መስጫ ድርጅቶችና የስራ ማከናወኛ ቦታዎች ያሉ የቤት ውስጥና የቤት ውጭ መገልገያ ተቋማት!
ለ) የኤሌክትሮኒክና የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎቶችን ጨምሮ የመረጃ፣ የመገናኛና ሌሎች አገልግሎቶች፡፡
2. ተዋዋይ መንግስታት በተጨማሪ ከዚህ በታች የተመለከቱትን በስራ ላይ ለማዋል ተገቢ እርምጃዎችን ይወስዳሉ፡፡
ሀ) ለሕዝብ ክፍት የተደረጉ ወይም የተመቻቹ ተቋማትንና አገልግሎቶችን ለመድረስ የሚያስችሉ ዝቅተኛ መስፈርቶችንና መመሪያዎችን ማዘጋጀት፣ በይፋ ማውጣትና ተግባራዊነታቸውን መቆጣጠር!
ለ) ለሕዝብ ክፍት የሆኑ አገልግሎቶችን በማመቻቸትና በማቅረብ ስራ ላይ የተሰማሩ የግል ድርጅቶች እነዚሁ አገልግሎቶች ለአካል ጉዳተኞች ጭምር ተደራሽነት እንዲኖራቸው አስፈላጊ የሆኑትን ጉዳዮች ሁሉ ግምት ውስጥ ማስገባታቸውን ማረጋገጥ!
ሐ) አካል ጉዳተኞችን በሚገጥሟቸው የተደራሽነት ችግሮች ዙሪያ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ወገኖች ስልጠና መስጠት!
መ) ለሕዝብ ክፍት በሆኑ ሕንፃዎችና ሌሎች መገልገያ ተቋማት ውስጥ በግልጽ የሚታዩ ምልክቶችን፣ ብሬሎችንና በቀላሉ አንብቦ ለመረዳት የሚያስችሉ ቅጾችን ማስቀመጥ ወይም ማቅረብ!
ሠ) የቀጥታ ድጋፍ ዓይነቶችንና መሪዎችን፣ አንባቢያንንም ሆነ በምልክት ቋንቋ አጠቃቀም የሰለጠኑ አስተርጓሚዎችን ጨምሮ ለሕዝብ ክፍት የሆኑ ሕንፃዎችንና ሌሎች መገልገያ ተቋማትን ተደራሽነት የሚያመቻቹ አማካዮችን ዝግጁ ማድረግ!
ረ) አካል ጉዳተኞች መረጃ የማግኘት ዕድል የተጠበቀላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሌሎች ተገቢነት ያላቸውን የእርዳታና የድጋፍ ዓይነቶችን ማስፋፋት!
ሰ) አካል ጉዳተኞች የመረጃን መረብን ጨምሮ በአዳዲስ የመረጃና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችና ሥርዓቶች የሚጠቀሙበትን ዕድል ከፍ ማድረግና!
ሸ) ለወደፊቱ በዝቅተኛ ዋጋ ሊቀርቡ የሚችሉበት ዕድል እስኪፈጠር ድረስ ምቹና ተደራሽነት ያላቸውን የመረጃና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችና ሥርዓቶች ዝግጅት፣ ልማት፣ አመራረትና ሥርጭት ከመነሻው ጀምሮ ማስተዋወቅ የሚል ዝርዝር ካስቀመጠው በመነሳት ይመስላል ኢትዮጵያም የህንጻ አዋጅ 624/2001በአንቀጽ 36 ማንኛውም ህንጻ ለአካል ጉዳተኞች በተሽከርካሪ ወንበር መንቀሳቀስ በሚያመች መለኩ እንዲገነባ፣ መጸዳጃቤቶችም ለአጠቃቀም በሚያመች መልኩ መሰራት እንዳለባቸው፤
ይህንኑ አዋጅ ለማስፈጸም በወጣው ደንብ ቁጥር 243/2003 /ሰ33/3፣ እና 34የህዝብ መገልገያ ህንጻዎችን አስመልክቶ በተደነገገው ሊፍቶቹ አካል ጉዳተኞች ያለምንም ችግር ሊጠቀሙባቸው እንዲችሉ፣ በአደጋ ጊዜ መውጫ እነሱን ታሳቢ ማድረግ ብቻ ሳይሆን መታጠቢያና ልብስ መቀየሪያ ቦታ እንዲያዘጋጁ፤ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ሲዘጋጁ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ አለማቀፋዊ ደረጃን ያሟላና አደናቃፊ ነገሮችን ያስወገደ፤ መሆን ይህንን ካላሟላ የመገልገያነት ፈቃድ ሊሰጠው እንደማይገባ ተደንግጎ ቢገኚም የክፍለ ከተማችንን ቅጥረ ግቢና ህንጻ ጨምሮ በከተማችን በጀት የሚሰሩ ረጃጅምና ለህዝብ አገልግሎት የሚገነቡና በስራ ላይ የሚገኙ ህንጻዎችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ተደርገው አለመሰራታቸው ሳያንስ የርማት ሀሳብ ሲሰጥም የሚመለከታቸው አካላት ጆሮ ዳባልበስ ብለው ጉዳዩ ከመወገድና ከመቀነስ ይልቅ እየባሰ መሄዱ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1152/2012ም በአንቀጽ 41/1/5/ በደነገገው ተቋማቱ አቅም በፈቀደ መገልገያ ህንጻዎችን መንሸራተቻ እንዲኖራቸው፤ የብሬልና የድምጽ ምልክቶች እንዲኖራቸው እንዲያደርጉ፤ ደንግጎ እናገኘዋለን፡፡
ስራን አስመልክቶ ኢትዮጵያ ስለአካልጉዳተኞች በአዋጅ 568/2000 ከመድሎ፣ እንዲጠበቁ፣ ድጋፍ እንዲደረግላቸው፣ አካል ጉዳተኚነታቸውን መሰረት ያደረገ ከልካይ መድሎ ቢደረግባቸው ጭብጥ ብቻ በማሲያዝ ለፍርድቤት ክስ እንዲያቀርቡ፤ በማህበር እንዲወከሉ መብቶች የያዘ ድንጋጌ በሀገሪቱ ባሉ ክልሎች ሁሉ ተፈጻሚነት እንዳለው፣ ነገር ግን ክልሎች ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት መመሪያወችን እንዲያወጡ በፈቀደው መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክሰርቪስ ቢሮ በ2005 መመሪያ አውጥቶ በሰራ ላይ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ የሲቪል ሰሪቪስ አዋጅ ቁጥር 1064ና በአዲስአበባ ከተማየመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 56/2010 በተመሳሳይ አንቀጽ 49 ለአካል ጉዳተኞች እጩ እና ተቀጣሪ ሰራተኞች የተሻለ ፈጻሚዎች እንዲሆኑ ልዩ ድጋፎች እንዲደረግላቸው ይደነግጋል፡፡
አለማቀፉ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ግን በይበልጥና በዝርዝር የሚከተለውን በአንቀጽ 27 አስቀምጧል-

Comments

Be the first to add a comment