በመርካቶ የሚገነባው የ2,500 ዘመናዊ ሱቆች ሜጋ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በመርካቶ ጣና ገበያ አካባቢ ከ10,000 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚያገኙበት እና 2,500 ዘመናዊ የንግድ ሱቆችን የሚያጠቃልል አዲስ የግንባታ ፕሮጀክት አስጀመረ።
1 ነጥብ 8 ሄክታር ስፋት ባለው መሬት ላይ በ10 ሳይቶች የሚከናወነው ይህ ፕሮጀክት ባለ 5 ወለል ሕንጻዎችን፣ በቂ የፓርኪንግ ቦታዎችን እና የከተማዋን ስታንዳርድ የጠበቁ ዘመናዊ መዋቅሮችን ያካተተ ነው።
የተቋሙ ገቢ ማሻሻያ፡ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ረሻድ ከማል በግንባታ ማስጀመሪያው ላይ እንደገለጹት፤ ኮርፖሬሽኑ ባደረገው ጠንካራ ሪፎርም ዓመታዊ ገቢውን ከነበረበት 300 ሚሊዮን ብር ወደ 12.5 ቢሊዮን ብር ማሳደግ ችሏል።
ለግንባታ ሲባል የፈረሱ የቀድሞዎቹን 230 ሱቆች ተክቶ የኮርፖሬሽኑን ገቢ ለማስቀጠል፣ ተጨማሪ 399 አዳዲስ ሱቆች በመርካቶ አዳራሽ ገበያ አካባቢ በአጭር ጊዜ ተገንብተው በዛሬው ዕለት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
ፕሮጀክቱ በዜሮ ኢንቨስትመንትና የግል ባለሀብቶችን አሳታፊ በማድረግ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ ታውቋል።
ግንባታው ለአዲስ አበባ ከተማ ኮሪደር ልማትና ዘመናዊ ገጽታ ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ሲሆን፤ ኮርፖሬሽኑ ብቁ ለሆኑ የግል አልሚዎች በጋራ ለመሥራት ጥሪ አቅርቧል።
@etconp