👉ለቢሾፍቱ ኤርፖርት ግንባታ በወር 16.5 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ እየቀረበ ነው ተባለ

🛩 ለቢሾፍቱ ኤርፖርት ግንባታ በወር የሚያስፈልገው የነዳጅ ድርሻ መጠን በልዩ ሁኔታ ተሰልቶ እየቀረበ መሆኑ ተገልጿል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ አጠገብ አቡሴራ በተባለ አካባቢ ለሚያስገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ (ኤርፖርት) ግንባታ ፕሮጀክት፣ በወር የሚያስፈልገው የነዳጅ መጠን በልዩ ሁኔታ ተሰልቶ 16.5 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ እየቀረበ መሆኑን የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

🛩 የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ግንባታ መሠረት ድንጋይ ጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አማካይነት መቀመጡ ይታወሳል፡፡ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኳንንት (ዶ/ር)፣ የቢሾፍቱ ኤርፖርት ትልቅ አገራዊ ፕሮጀከት መሆኑንና ራሱን የቻለ የነዳጅ ድልድል ሥሌት እንደተሠራለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

🛫 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ለዚህ አገራዊ ሜጋ ፕሮጀክት ከ17 ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ በወር ጥያቄ ማቅረቡን፣ ሆኖም አገሪቱ ከምታስገባው ነዳጅ ጋር በማመጣጠን 16.5 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ የድርሻ ሥሌትም በቀን ከሚቀርበው አንፃር በአማካይ ተሰልቶ የተፈቀደ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለዚህም ሲባል የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች አስቀድመው ታንከር እንዲቀብሩ፣ ከኮንትራክተሮች ጋር ውል እንዲገቡ መደረጉን ጨምረው አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሦስት ኮንትራክተሮች በፕሮጀከቱ እየተሳተፉ መሆናቸውን፣ ለእያንዳንዳቸው ሰባት ትልልቅ ኩባንያዎች ነዳጅ እንዲያቀርቡ ውል መገባቱን ተናግረዋል፡፡ ትልልቆቹ ኩባንያዎች የተመረጡት ያላቸውን የሎጂስቲክስ አቅም መሠረት ተደርጎ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ከሁለት ወይም ከሦስት ኩባንያዎች ጋር ብቻ የመሥራት ፍላጎት እንደነበረው፣ ነገር ግን በነዳጅ ሥርጭት ላይ ሊፈጠር የሚችል ችግርን ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በማስረዳት የአቅራቢዎች ቁጥር ከፍ እንዲል መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ወደ አገር ውስጥ ከሚገባው ነዳጅ 84 በመቶው በቀጥታ ለሕዝብ አገልግሎት እንደሚውልና ቀሪው ለትልልቅ ፕሮጀከቶች የሚመደብ መሆኑን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ለቢሾፍቱ ኤርፖርት እየቀረበ ያለው ነዳጅ በልዩ ሁኔታ መደልደሉንና ቀጥታ ተጠቃሚ የሆነውን ማኅበረሰብ ድርሻ እንዳይሻማ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ምን ያህል ነዳጅ እንደሚያስፈልገው ጥናት ተደርጎ መፈቀዱን የተናገሩት ደስታው (ዶ/ር)፣ የሥራ ሒደቱ ሲጠናከርና የተሸከርካሪዎች ብዛት ሲጨምር የሚቀርበው ድርሻ ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

🛫 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ካቀረበው ፍላጎት አንፃር በአሁኑ ወቅት እየቀረበ ያለው በቂ ነው ማለት አይቻልም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በአገር አቅም የሚቻለውን ያህል ለፕሮጀከቱ እየተሠራጨ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀከቱ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው አገራዊ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሆኖም ከነዳጅ ጋር በተያያዘ ችግር ሥራው እንዲቆም እንደማይደረግ ግን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ከአዲስ አበባ በደቡብ ምሥራቅ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቢሾፍቱ ከተማ እየተገነባ ያለው ኤርፖርቱ፣ ከአሥር ዓመት በኋላ ሲጠናቀቅ እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን በዓመት የማስተናገድ አቅም እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ብቻ በዓመት 60 ሚሊየን መንገደኞችን ማስተናገድ እንደሚያስችል ተነግሯል፡፡

በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ባለፉት ዓመታት በተሠሩለት የማስፋፊያ ሥራዎች ምክንያት በእዚህ ዓመት 21 ሚሊዮን የሚጠጉ መንገደኞችን ያስተናግዳል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቢሾፍቱን ኤርፖርት ግንባታን በፍጥነት መጀመር ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ሲገልጹ፣ በየዓመቱ የመንገደኞች ቁጥር በሁለት ሚሊዮን የሚጨምር ከሆነ ከሁለትና ከሦስት ዓመታት በኋላ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ተጨማሪ መንገደኞችን ማስተናገድ እንደማይችል አስታውቀው ነበር፡፡

‹‹ያንን ችግር ከወዲሁ ተገንዝበን ዛሬ ሥራ ካልጀመርን፣ የአፍሪካ ኩራት ታላቁ አየር መንገድ የሚለውን ስም ተጎናፅፈን ማቆየት እንቸገራለን፡፡ በዚህም ለነገ ዛሬ አስቀድሞ መሥራት በማስፈለጉ ይህ ውሳኔ ተወስኗል፤›› ብለዋል፡፡

🛫 የቢሾፍቱ ኤርፖርት አጠቃላይ ግንባታ ወጪ 12.5 ቢሊዮን ዶላር መገመቱን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ለሪፖርተር መግለጹ አይዘነጋም፡፡

@etconp

Comments

Be the first to add a comment