👉የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር 9ኛውን ዓመታዊ የመንገድ ምርምር ኮንፈረንስ አካሄደ

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አዳዲስ እና ውጤታማ ቴክኖሎጂዎችን ለአገር ውስጥ ባለሙያዎች እና ተቋራጮች ለማስተዋወቅ ያዘጋጀው 9ኛው ዓመታዊ የመንገድ ምርምር ኮንፈረንስ የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር በመንገድ ምርምር ማዕከል በመገኘት ተሳትፏል።

በኮንፈረንሱ ላይ ዘላቂ እና ወጪ ቆጣቢ የመንገድ ግንባታ አማራጮች፣ የቁሳቁስ ጥራት ማሻሻያዎች እና ዘመናዊ የጥገና ዘዴዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ ከተነሱ ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የሲሚንቶ ኮንክሪት ንጣፎች (Cement Concrete Pavements) እንደ ዘላቂ አማራጭ አገልግሎት ላይ መዋል የሚችሉበት ሁኔታ ይጠቀሳል። በውጭ ምንዛሬ ከሚገባው የቢቱመን ንግድ ጥገኛ ላለመሆን የጠንካራ መንገድ ንጣፎችን አጠቃቀም ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል።

እንዲሁም ለታችኛው ሽፋን (Subbase) በሲሚንቶ የተረጋጉ የሀገር ውስጥ ተፈጥሯዊ ጠጠር ቁሳቁሶችን መጠቀም የንጣፉን መዋቅራዊ ቁጥር ከፍ እንደሚያደርገው ተገልጿል። ይህ አሠራር የአስተዳደሩን ዝርዝር መግለጫዎች እንዲሻሻሉ የሚያደርግ በመሆኑ፣ ሥራ ተቋራጮች የተሻሻሉ የመንገድ መሠረት ግንባታ ዘዴዎችን እንዲከተሉ ጥሪ ቀርቧል።

ለወደፊት የመንገድ እድሳት ሥራዎች ሙሉ ጥልቀት ያለው ማገገሚያ (Full Depth Reclamation - FDR) ቴክኖሎጂን መቀበል ጊዜንና ገንዘብን ስለሚቆጥብ የማይቀር መሆኑ ተወስቷል።

ይህንን ቴክኖሎጂ በሥራ ላይ ለማዋል እንደ ፓግሚል ማሽን ያሉ አዳዲስ ማሽነሪዎች የሚጠየቁ ሲሆን፣ የሲሚንቶ ማረጋጋት ሂደቱ ንጣፉ እንዳይጠናከር በ2 ሰዓታት ውስጥ ተቀላቅሎ መጠናቀቅ እንዳለበት አጽንኦት ተሰጥቶበታል።

በኮንፈረንሱ የተገኙ ባለሙያዎች እና ተቋራጮች በተለይም የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች ተወዳዳሪ ለመሆን እና አዳዲስ ማሽነሪዎችን ለመለማመድ ፎርማኖቻቸውን እና ኦፕሬተሮቻቸውን አስቀድመው ማዘጋጀት እንደሚገባቸው ተመላክቷል።

ማዕከሉ ያቀረባቸው እነዚህ የምርምር ውጤቶች የሀገሪቱን የመንገድ አውታር ደህንነቱ የተጠበቀ እና ቀልጣፋ ለማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ታምኖበታል።

@etconp

Comments

Be the first to add a comment