👉በአዲስ አበባ ብቻ 141 ሰዎች በሕንፃ ግንባታ ሥራ ላይ በደረሰ አደጋ ሕይወታቸው ማለፉ ተገለጸ🚧ከ 2015 እስከ 2017 በጀት ዓመት በተሰራ ጥናት መሠረት በሁለት ዓመት ውስጥ ብቻ 141 ሰዎች በሕንጻ የግንባታ ሥራ ላይ በደረሰ አደጋ ሕይወታቸው ማለፉን የአዲስ አበባ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ለአሐዱ አስታውቋል።
ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች በሁሉም የእድሜ ክልልና ፆታ የሚገኙ መሆናቸውን የገለጹት የባለስልጣን መስሪያቤቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አበበ እሸቱ ናቸው።
በተደረገው ጥናት መሠረት የሞታቸው መንስኤ ተብለው የተለዩት፤ የመጀመሪያው ጥንቃቄ ባልተሞላበት መንገድ የደህንነት ቀበቶ፣ ጫማ እና ኮፍያ የመሳሰሉትን ሳያደርጉ ሲሰሩ የነበሩ ሠራተኞች ከከፍታ ላይ መውደቃቸው ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ከዚህ ሌላም በግንባታው ቦታ ላይ በሚያጋጥም የኤሌክትሪክ አደጋ ሲሆን፤ የተላጠ ኤሌክትሪክ በሚይዙበት ወቅት ወይም መብራት ሳያጠፉ በሚሰሩበት ጊዜ የሚከሰት እንደሆነ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከላይ ብሎኬት ወይም ድንጋይ በመውደቁ ከሥር ያለውን ባለሙያ ሔይወት ያጠፋበት ሁኔታ ስለመኖሩ ም/ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
ሕይወታቸውን ካጡ ዜጎች መካከል አብዛኞቹ የሕንፃ ግንባታ ሠራተኞች መሆናቸውን አንስተው፤ አንዳንዶች ግን ህንፃውን ለመጎብኘት ወይም ለመግዛት የሚሄዱ ሰዎች ላይ ጭምር አደጋው መከሰቱን ገልጸዋል።
ም/ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም እነዚህ አደጋዎችም በቀላሉ ጥንቃቄ ቢደረግ ኖሮ መከላከል እና የሞት አደጋን ማስቀረት የሚቻልበት ሁኔታ እንደነበረ አስረድተዋለ።
በመሆኑም የሕንፃ ግንባታ ደህንነትን በተመለከተ በሰፊው እየተሰራ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፤ ከበፊቱ የሞት አደጋ እየቀነሰ ስለመምጣቱ ተናግረዋል።
Via አሐዱ ሬዲዮ
@etconp