የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
በሰዎች መነገድ ወይም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚሳተፉ የአዘዋዋሪዎች ማንነት
በኢትዮጵያ የተካሄዱ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከማንነት፣ ከአሰራርና በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሂደት ከሚኖራቸው ሚና አንፃር አዘዋዋሪዎች በአምስት ሊመደቡ ይችላሉ፡፡
1. በመጀመሪያው ምድብ የሚገኙት ተጠቂዎቹ በሚኖሩባቸው ማህበረሰቦች ውስጥ የሚገኙ የአካባቢ ደላሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ደላሎች የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና በሌሎች ዘዴዎች ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አመቺ ሁኔታ የመፍጠር እና ተጋላጭ ግለሰቦችን በመለየት የዝውውር ሂደቱን የመጀመረ ሚና አላቸው፡፡ ብዙውን ጊዜ የአካባቢ ደላሎች የሚንቀሳቀሱት የምልመላ እና በመደበኛና ኢ-መደበኛ መንገዶች የማዘዋወር ሂደቱን ከሚያከናውኑ ሌሎች አዘዋዋሪዎች ጋር በመሆን ነው፡፡
2. በሁለተኛው ምድብ ያሉት ደግሞ ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ሰዎችን የሚያዘዋውሩና ድንበር የሚያሻግሩ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ እነዚህ አዘዋዋሪዎች ሰዎችን በቡድን ከአካባቢ ደላሎች ተቀብለው ለሌሎች ተመሳሳይ አዘዋዋሪዎች በማስተላለፍ በቅብብሎሽ የሚያደርሱ ናቸው፡፡
3. በሶስተኛ ደረጃ የሚገኙት ደግሞ በትላልቅ ከተሞች የሚንቀሳቀሱና ወደ መዳረሻ ቦታዎች በመደበኛ የጉዞ መስመሮች የሚደረገውን ጉዞ የማቀላጠፍ እና ቅጥር የማመቻቸት አላፊነት የሚወስዱ ደላሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ደላሎች ከአካባቢ ደላሎች ሰዎችን ተቀብለው በመዳረሻ አገራት ለሚገኙ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች ያስተላልፋሉ፡፡ በዚህም ከሥራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋር ተመሳሳይ ነገርግን ህገወጥ የሆነ ስራ ይሰራሉ፡፡
4. በአራተኛው ምድብ የሚገኙት ከስደት ተመላሾችና ቤተሰቦቻቸው ሲሆኑ ሌሎች ሰዎች እነሱ ወደነበሩበት አገር በመሄድ እንዲቀጠሩ በግለሰብ ደረጃ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በግል ትውውቅ ወደ ውጭ አገር ለመጓዝ የሚሹ ዘመድና ጎረቤቶችን ከማገዝ ባለፈ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመደበኛነት በመያዝ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡
5. በመጨረሻ የምናገኛቸው በመዳረሻ አገራት የሚገኙ እና በመደበኛና ኢ-መደበኛ መንገዶች በመዳረሻ ቦታዎች የሰዎች ዝውውር ላይ የተጠመዱ አዘዋዋሪዎች ናቸው፡፡ ከተለያዩ ምንጮች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው እነዚህ አዘዋዋሪዎች በመዳረሻ አገራት የሚገኙ ደላሎች፣ የስራና ሰራተኛ አገናኝ ድርጅቶች ወይም ቀደም ብለው የሕገወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ተጠቂዎችን በማታለል፣ በማስገደድ ወይም በማስፈራራት ለብዝበዛ በቀጥታ የሚያጋልጡ አዘዋዋሪዎች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜም በብዝበዛው ሂደት ቀጥተኛ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
ቸር ሰንብቱ!!
ፌናን ተጊበሉ
የካቲት 19/2013 ዓ.ም
Comments
Be the first to add a comment