👉በአዲስ መልክ ተዘጋጅተው በጸደቁ የኢትዮጵያ የህንፃ ኮድ ስታንዳርዶች  ላይ የባለድርሻ አካላት ምክክር ተካሄደ፡፡

🚧የግንባታ ደህንነት በአጋጣሚ የሚረጋገጥ ሳይሆን በስታንዳርድ እና በኮድ ይሁነኝ ተብሎ የሚከናወን ነው። የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17 ቀን 2018 ዓ.ም. – የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን በአዲስ መልክ ተሻሽለውና ተዘጋጅተው የጸደቁ የኢትዮጵያ የህንፃ ኮድ ስታንዳርዶች ላይ ከመንግስት ተቋማት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዘርፉ ቋሚ ኮሚቴ አባላት፥ ከሙያ ማኅበራት፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከግሉ ዘርፍ እና ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በከተማና መሠረተልማት ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት የትምጌታ አስራት ዶ/ር መድረኩን ሲከፍቱ ባስተላለፉት መልዕክት የብሄራዊ ስታንዳርድ እና ኮድ ትግበራ የዘርፉ ግንባታ ዋና ምሶሶ አድርጐ ማየት እንደሚገባ ገልፀዋል።

የምክክር መድረኩ በሀገሪቱ የግንባታ ዘርፍ እየታዩ ያሉ ፈጣን ለውጦችን፣ የቴክኖሎጂ እድገቶችን፣ የከተሞች መስፋፋትን እና እየጨመረ የመጣውን የህንፃ ደህንነትና ጥራት ፍላጎት በማገናዘብ የተዘጋጁትን አዳዲስ እና የተሻሻሉ ኮዶች ለማስተዋወቅና ግብዓት ለመሰብሰብ ታስቦ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ 48 ኮድና ስታንዳርድ ተሻሽለው እና በአዲስ መልክ  ተዘጋጅተዋል። ኮዶቹ የመዋቅር ዲዛይን፣ የመሬት መንቀጥቀጥ መቋቋም፣ የጂኦቴክኒክ ዲዛይን፣ የውሃ አቅርቦትና ፍሳሽ ስርዓት፣ የኤሌክትሪክና የሜካኒካል ስርዓቶች፣ የእሳት፣ የሥራ ቦታ ጤናና ደህንነት፣ የህንፃ ፋሲሊቲ ማኔጅመንት እና የ(አሳንሰር) ቨርቲካል ትራንስፖርት ስርዓቶችን ጨምሮ የግንባታውን ዘርፍ በስፋት ይሸፍናሉ።

የኮድ ማሻሻያ ሥራው በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን መሪነት  እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂና ቢውልት ኢንቫይሮመንት ኮሌጅ ፈጻሚነት የተከናወነ ሲሆን ከ128 በላይ ባለሙያዎች በዝግጅቱ ተሳትፈዋል።

የአማካሪው ቡድን አስተባባሪ የኢሳያስ ገ|ዮሃንስ (ዶ/ር) በአዲስ መልክ ተዘጋጅተው የጸደቁትን  ኮድና ስታንዳርድ በ5 በመክፍል ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ከተሳታፊዎች አስተያየቶችና የግልፅነት ጥያቄዎች ቀርበዋል።

የፀደቁት ኮድና ስታንዶች አስመልክቶ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ተከታታይነት ያላቸው áˆľáˆáŒ áŠ“ እንደሚያስፈልግ፥ የፀደቁት ኮዶች በስራ ላይ ባለሙያው እንዲጠቀመው ተግባራዊ እንዲሆኑ ከፍተኛ ክትትልና ቅጣት አስፈላጊ መሆኑ፥ ዝርዝር የሆነ ጋይድ ላይን ቢዘጋጅ የሚሉ ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን የተሻሻሉት ኮዶች የግንባታ ጥራትን፣ ደህንነትን፣ ዘላቂነትን እና የዘርፉን ተወዳዳሪነት በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸውም  ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።

እንዲሁም ኮዶቹ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆኑ የአቅም ግንባታ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መሠጠት ለዚህም እና የተቀናጀ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

በተሰጡት አስተያየቶች ማብራሪያ የሠጡት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ ዶ/ር ስልጠና በክሊፕ ተዘጋጅቶ ለተጠቃሚ በቀላሉ ለማድረስ እራሱን የቻለ እቅድ በመንደፍ በቀጣይ የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል።

የምክክር መድረኩ ተሻሽለው የጸደቁትን የኢትዮጵያ የህንፃ ኮድና  ስታንዳርዶች ወደ ተግባር ለማሸጋገር እና በግንባታው ዘርፍ የህግ ተገዢነትን፣ ጥራትን እና ደህንነትን ለማጠናከር ጠቃሚ መድረክ መሆኑ ተገልጻል፡፡

በመድረኩ ማጠቃለያ በኮድናስታንዳርድ ማሻሻያ ውስጥ አሻራቸውን ያሳረፉ ተቋማት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፥ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት እና በተለያየ ደረጃ ተሳታፊ ለነበሩ ባለሙያዎች የእውቅና  እና የምስጋና ስርተፊኬት ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን

@etconp

1 comment

እኔ እንደ አንድ የህንጻ ሹም ሰራተኛ ይህንን አድስ ስታንዳርድ እና ኮዶችን እንደት ማገኘት እችላለሁ ?