የባሕር ዳር  ዓባይ ወንዝ ድልድይ መዳረሻ መንገድ ግንባታ ሥራ 95 በመቶ ተጠናቀቀ

በሀገራችን በዓይነቱ እና በዘመናዊነቱ የመጀመሪያ የኾነው የአዲሱ የባሕር ዳር ዓባይ ወንዝ ድልድይ መዳረሻ መንገድ ግንባታ ሥራ 95 በመቶው የተጠናቀቀ ሲኾን፥ ቀሪ ውስን ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ ነው።

ዋናው የመዳረሻ መንገድ መነሻውን ከሄኒ ጋርደን መገንጠያ አድርጎ እስከ ዘንዘልማ ጎንደር መውጫ ድረስ የሚዘልቅ ሲኾን፥ በአጠቃላይ 4 ነጥብ 72 ኪሎ ሜትር ይረዝማል። መንገዱ የአውቶቡስ እና የታክሲ መቆሚያዎችን ጨምሮ 59 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲኾን፥ በግራና በቀኝ 3 ተሽከርካሪዎችን በተመሳሳይ ጊዜ (በአጠቃላይ 6 ተሽከርካሪዎችን) የማስተናገድ አቅም አለው።

ከዚህም ባለፈ የመኪና ማቆሚያ ቦታ፣ የእግረኛ መንገድ፣ የመንገድ ዳር ምልክቶች እና መብራቶች እንዲሁም የመሐል አካፋይ እና የመንገድ ዳር አረንጓዴ ሥፍራዎችን አካትቶል።

እስከ አሁን ባለው የግንባታ ሥራ ከአፈር ቆረጣ እና ሙሌት፣ የመፋሰሻ ቱቦዎች ዝርጋታ፣ የሰብቤዝ እና ቤዝኮርስ ማንጠፍ፣ ሁለት ደረጃ የአስፓልት ንጣፍ፣ የቀለም፣ የእግረኛ መንገድ ጋር የተያያዙ ዋና ዋና ሥራዎች ተጠናቅቀዋል። ከዚህም ባለፈ 800 ሜትር የሚረዝመው እና 4 መኪና ጎን ለጎን ማስተናገድ የሚያስችለው የቤዛዊት መንገድ እና መወጣጫ ድልድዮች ግንባታ ሥራ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተጠናቅቋል።

አሁን ላይ የፕሮጀክቱ ቀሪ ሥራዎች የዘንዘልማ ጎንደር መውጫ መንገድ መጋጠሚያ፣ ውስን የአስፓልት ድራቢዎች፣ የመንገድ ዳር መብራት እንዲሁም ትናንሽ የመገንጠያ መንገዶች ግንባታ በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱን ሀፍኮን ኮንስትራክሽን ከክሮስላንድ ኮንስትራክሽን ጋር በጥምረት እያከናወኑ ሲኾን፥ ስታዲያ ኢንጅነሪንግ የማማከር እና የቁጥጥር ሥራውን በማከናወን ላይ ይገኛል። ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚኾን 825 ሚሊዮን ብር በፌደራል መንግሥት ተመድቧል።

መዳረሻ መንገዱ የኢትዮ ሱዳን ዋና መስመር የሆነው የአዲስ አበባ - ባህርዳር - ጎንደር-መተማ  መንገድ አንዱ ክፍል ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረውን አዲሱንና ዘመናዊውን የዓባይ ወንዝ ድልድይ ከዋናው አውራ ጎዳና ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ በመሆኑ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ አለው።

ከዚህም ባሻገር በአገልግሎት ብዛት የተጎዳውን  ነባር  የባህር ዳር ዓባይ ወንዝ ድልድይ የትራፊክ ጫና ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ያስተነፍሳል ተብሎ ይጠበቃል።

Via ERA

@etconp

Comments

Be the first to add a comment