ስለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምን ያህል ያውቃሉ? እስኪ ስለኮሚሽኑ እነዚህን ጠቃሚ ነጥቦች እናጋራችሁ!
1/ የኮሚሽኑ መቋቋም እና ተጠሪነት
• መቋቋም፦ ኮሚሽኑ የከተማው አስተዳደር መሥሪያ ቤት ሆኖ በአዋጅ ቁጥር 75/2014 ተቋቁሟል።
• ተጠሪነት፦ የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለከተማው ምክር ቤት ነው።
• ነፃነት፦ ኮሚሽኑ ተግባሩን ሲያከናውን ከማንኛውም ሰው ወይም አካል ጣልቃ ገብነት ነፃ ነው።
2/ የኮሚሽኑ አቋምና አመራር
• መዋቅር፦ ኮሚሽኑ በከንቲባው አቅራቢነት በምክር ቤት የሚሾሙ ኮሚሽነር እና ምክትል ኮሚሽነሮች እንዲሁም አስፈላጊ የሥራ ክፍሎችና ሠራተኞች ይኖሩታል።
• የሥራ ዘመን፦ የኮሚሽነሩና የምክትል ኮሚሽነሩ የሥራ ዘመን 6 ዓመት ሲሆን፣ ለተጨማሪ አንድ የሥራ ዘመን ብቻ ድጋሚ ሊሾሙ ይችላሉ።
• ከኃላፊነት መነሳት፦ ከፈቃዳቸው ውጭ ከሥራ የሚነሱት በሥነ-ምግባር ጉድለት፣ በችሎታ ማነስ፣ በጤና ችግር ወይም ለጡረታ ሲበቁ ብቻ ሲሆን፣ ይህም በምክር ቤት ተጣርቶ በአብላጫ ድምፅ መፅደቅ አለበት።
3/ የኮሚሽኑ ዓላማዎች
1. ሙስናን የማይታገስ የነቃ ኅብረተሰብ መፍጠር።
2. የሙስና ወንጀልንና ብልሹ አሠራርን መከላከል።
3. ነዋሪው የፀረ-ሙስና ትግል ባለቤት እንዲሆን ማድረግ።
4. ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር ማስፈን።
5. ተቋማዊ አቅምን መገንባት።
4/ ዋና ዋና ሥልጣንና ተግባራት
• ፖሊሲና ስትራቴጂ፦ ከተማ አቀፍ የፀረ-ሙስና ፖሊሲ ያዘጋጃል፣ ሲጸድቅም ይተገብራል።
• ሥልጠና፦ ተሿሚዎችና ሠራተኞች ሥራ ከመጀመራቸው በፊት የሥነ-ምግባር ሥልጠና እንዲወስዱ ያደርጋል።
• ጥናትና ማሻሻያ፦ ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ አሠራሮችን በማጥናት የመፍትሔ ሃሳብ ያቀርባል፤ ተግባራዊ ባላደረጉት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ለሕግ አካል ያቀርባል።
• ቅድመ-መከላከል፦ ሙስና ሊፈጸም መሆኑን ሲጠረጥር ድርጊቱ ከመፈጸሙ በፊት ጣልቃ በመግባት ያስቆማል።
• የሀብት ምዝገባ፦ የተሿሚዎችንና ሠራተኞችን ሀብት ያስመዘግባል፣ ትክክለኛነቱን ያረጋግጣል፣ መረጃውንም ለሕዝብ ተደራሽ ያደርጋል። ለዚህም ሶፍትዌር ያበለጽጋል።
• የጥቅም ግጭት፦ የጥቅም ግጭትን ለመከላከል ሥርዓት ይዘረጋል።
• ዕውቅናና ሽልማት፦ በፀረ-ሙስና ትግል ውጤታማ የሆኑ አካላትን ያወዳድራል፣ ይሸልማል።
• ክትትል፦ የሥነ-ምግባር ደንቦችን ያዘጋጃል፣ የፀረ-ሙስና ሕጎች መከበራቸውን ያረጋግጣል።
• ሪፖርት መቀበል፦ ከምርመራና ክስ መሥራች አካላት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ይቀበላል።
5/ የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍሎች አደረጃጀት
• ኮሚሽኑ በመሥሪያ ቤቶችና በልማት ድርጅቶች ውስጥ የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍሎችን ያደራጃል።
• እነዚህ ክፍሎች ተጠሪነታቸው ለኮሚሽኑ ነው።
• የእነዚህ ክፍሎች ኃላፊዎችንና ሠራተኞችን የመመደብ፣ የመቅጠርና የማሰናበት ሥልጣን የኮሚሽኑ ነው (ከተቋማቱ ማኔጅመንት ጋር በመመካከር)።
6/ ግንኙነትና ሌሎች ጉዳዮች
• የሥራ ግንኙነት፦ ከፌደራል፣ ከክልልና ከድሬዳዋ አስተዳደር ኮሚሽኖች ጋር የቴክኒክ ድጋፍ፣ የዕቅድና የሪፖርት ልውውጥ ያደርጋል።
• ሕጋዊ ሰውነት፦ ኮሚሽኑ የንብረት ባለቤት መሆን፣ ውል መዋዋል፣ መክሰስና መከሰስ ይችላል።

Comments

Be the first to add a comment